ምዕራፍ 9

ነገር ግን ተጨንቃ ለነበረች ጨለማ አይሆንም። በመጀመሪያው ዘመን የዛብሎንንና የንፍታሌምን ምድር አቃለለ፤ በኋለኛው ዘመን ግን በዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ ያለውን የአሕዛብን ገሊላ ያከብራል።
2 ፤ በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።
3 ፤ ሕዝብን አብዝተሃል፥ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፥ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል።
4 ፤ በምድያም ጊዜ እንደ ሆነ የሸክሙን ቀንበር የጫንቃውንም በትር የአስጨናቂውንም ዘንግ ሰብረሃል።
5 ፤ የሚረግጡ የሰልፈኞች ጫማ ሁሉ፥ በደምም የተለወሰ ልብስ ለቃጠሎ ይሆናል፥ እንደ እሳት ማቃጠያም ሆኖ ይቃጠላል።
6 ፤ ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።
7 ፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍፃሜ የለውም። የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል።
8 ፤ ጌታ በያዕቆብ ላይ ቃልን ሰደደ፥ በእስራኤልም ላይ ወደቀ።
9
10 ፤ በትዕቢትና በልብ ኵራት። ጡቡ ወድቆአል፥ ነገር ግን በተወቀረ ድንጋይ እንሠራለን፤ የሾላ ዛፎች ተቈርጠዋል፥ ነገር ግን ዝግባን እንተካባቸዋለን የሚሉ በኤፍሬምና በሰማርያ የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ ያውቃሉ።
11 ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ላይ ተቋቋሚ ያስነሣበታል፥
12 ፤ ጠላቶቹን ሶርያውያንንም ከምሥራቅ፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከምዕራብ ያንቀሳቅስበታል፤ እስራኤልንም በተከፈተ አፍ ይበሉታል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
13 ፤ ሕዝቡ ግን ወደ ቀሠፋቸው አልተመለሱም፥ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን አልፈለጉም።
14 ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ራስና ጅራትን፥ የሰሌኑን ቅርንጫፍና እንግጫውን በአንድ ቀን ከእስራኤል ይቆርጣል።
15 ፤ ሽማግሌውና ከበርቴው እርሱ ራስ ነው፤ በሐሰትም የሚያስተምር ነቢይ እርሱ ጅራት ነው።
16 ፤ ይህን ሕዝብ የሚመሩ ያስቱአቸዋል፤ ተመሪዎቹም ይጠፋሉ።
17 ፤ ሰው ሁሉ ዝንጉና ክፉ ሠሪ ነውና፥ አፍም ሁሉ ስንፍናን ይናገራልና ስለዚህ ጌታ በጕልማሶቻቸው ደስ አይለውም፥ ለድሀ አደጎቻቸውና ለመበለቶቻቸውም አይራራም። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
18 ፤ ክፋት እንደ እሳት ይቃጠላል፤ ኵርንችቱንና እሾሁን ይበላል፤ ጭፍቅ የሆነውንም ዱር ያቃጥላል፥ ጢሱም ተትጐልጕሎ እንደ ዓምድ ይወጣል።
19 ፤ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቍጣ ምድር ተቃጥላለች፤ ሕዝቡም እሳት እንደሚበላው እንጨት ሆኖአል፤ ሰውም ለወንድሙ አይራራም።
20 ፤ ሰው በቀኙ በኩል ይነቅላል ይራብማል፤ በግራም በኩል ይበላል አይጠግብምም፤ እያንዳንዱም የክንዱን ሥጋ ይበላል፤
21 ፤ ምናሴ ኤፍሬምን ኤፍሬምም ምናሴን ይበላል፤ እነርሱ በአንድነት የይሁዳ ጠላቶች ይሆናሉ። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፥ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።