ምዕራፍ 33

አንተ ሳትጠፋ የምታጠፋ፥ በአንተም ላይ ወንጀል ሳይደረግ ወንጀል የምታደርግ ወዮልህ! ማጥፋትን በተውህ ጊዜ ትጠፋለህ፤ መወንጀልንም በተውህ ጊዜ ይወነጅሉሃል።
2 ፤ አቤቱ፥ ማረን፤ አንተን ተማምነናል፤ ጥዋት ጥዋት ክንድ በመከራም ጊዜ ማዳን ሁነን።
3 ፤ ከፍጅት ድምፅ ወገኖች ሸሹ፥ በመነሣትህም አሕዛብ ተበተኑ።
4 ፤ አንበጣ እንደሚሰበስብ ምርኮአችሁ ትሰበሰባለች፥ ኩብኩባም እንደሚዘልል ሰዎች ይዘልሉበታል።
5 ፤ እግዚአብሔር በአርያም ተቀምጦአልና ከፍ ከፍ አለ፤ ጽዮንን በፍርድና በጽድቅ ሞላት።
6 ፤ የዘመንህም ጸጥታ፥ የመድኃኒት ብዛት፥ ጥበብና እውቀት ይሆናል፤ እግዚአብሔርን መፍራት መዝገቡ ነው።
7 ፤ እነሆ፥ ኃይለኞቻቸው በሜዳ ይጮኻሉ፤ የሰላም መልእክተኞች መራራ ልቅሶ ያለቅሳሉ።
8 ፤ መንገዶች ባድማ ሆኑ፥ ተላላፊም ቀረ፤ እርሱም ቃል ኪዳንን አፈረሰ ከተሞችንም ናቀ ሰውንም አልተመለከተም።
9 ፤ ምድሪቱ አለቀሰች ከሳችም፤ ሊባኖስ አፈረ ጠወለገም፤ ሳሮን እንደ ምድረ በዳ ሆነ፤ ባሳንና ቀርሜሎስ ቅጠላቸውን አረገፉ።
10 ፤ አሁን እነሣለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ አሁን እከበራለሁ፤ አሁን ከፍ ከፍ እላለሁ።
11 ፤ ገለባን ትፀንሳላችሁ፥ እብቅንም ትወልዳላችሁ፤ እስትንፋሳችሁ የምትበላችሁ እሳት ናት።
12 ፤ አሕዛብም እንደ ተቃጠለ ኖራ፥ ተቈርጦም በእሳት እንደ ተቃጠለ እሾህ ይሆናሉ።
13 ፤ እናንተ በሩቅ ያላችሁ የሠራሁትን ስሙ፥ እናንተም በቅርብ ያላችሁ ኃይሌን እወቁ።
14 ፤ በጽዮን ያሉ ኃጢአተኞች ፈሩ፤ መንቀጥቀጥ ዝንጉዎቹን ያዘ፤ ከምትበላ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ? ለዘላለምም ከምትነድድ እሳት ጋር መኖርን የሚችል ከእኛ ማን አለ?
15 ፤ በጽድቅ የሚሄድ ቅን ነገርንም የሚናገር፥ በሽንገላ የሚገኝ ትርፍን የሚንቅ፥ መማለጃን ከመጨበጥ እጁን የሚያራግፍ፥ ደም ማፍሰስን ከመስማት ጆሮቹን የሚያደነቍር፥ ክፋትንም ከማየት ዓይኖቹን የሚጨፍን ነው።
16 ፤ እርሱ ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣል፤ ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራም ይሰጠዋል፥ ውኃውም የታመነች ትሆናለች።
17 ፤ ዓይኖችህ ንጉሥን በውበቱ ያዩታል፤ እነርሱም በሩቅ ያለች ምድርን ያዩአታል።
18 ፤ ልብህም። ጸሐፊ ወዴት አለ? መዛኝስ ወዴት አለ? ግንቦቹንስ የቈጠረ ወዴት አለ? ብሎ የሚያስፈራ ነገር ያስባል።
19 ፤ ጨካኝን ሕዝብ፥ ቋንቋው ለማስተዋል ጥልቅ የሆነውንና አንደበቱ ለማስተዋል ጸያፍ የሆነውን ሕዝብ፥ አታይም።
20 ፤ የበዓላችንን ከተማ ጽዮንን ተመልከት፤ ዓይኖችህ የሰላም ማደሪያ፥ ካስማውም ለዘላለም የማይነቀል አውታሩም ሁሉ የማይበጠስ፥ የማይወገድ ድንኳን የሆነውን ኢየሩሳሌምን ያያሉ።
21 ፤ እግዚአብሔር በዚያ የሰፉ ወንዞችና የመስኖች ስፍራ ሆኖ ከእኛ ጋር በግርማ ይሆናል፤ የሚቀዘፉ መርከቦች አይገቡባትም፥ ታላላቆችም መርከቦች አያልፉባትም።
22 ፤ እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፥ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፥ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ እርሱ ያድነናል።
23 ፤ ገመዶችህ ላልተዋል፥ ደቀላቸውንም አላጸኑም፥ ሸራውንም መዘርጋት አልቻሉም። በዚያም ጊዜ የብዙ ምርኮ ብዝበዛ ተከፈለ፤ አንካሶች እንኳ ብዝበዛውን በዘበዙ።
24 ፤ በዚያም የሚቀመጥ። ታምሜአለሁ አይልም፥ በእርስዋም ለሚቀመጡ ሰዎች በደላቸው ይቅር ይባልላቸዋል።