ምዕራፍ 34

እናንተ አሕዛብ ሆይ፥ ቅረቡ፥ ስሙ፤ እናንተ ወገኖች ሆይ፥ አድምጡ፤ ምድርና ሙላዋ፥ ዓለምና ከእርስዋ የሚወጣ ሁሉ ይስሙ።
2 ፤ የእግዚአብሔር ቍጣ በአሕዛብ ሁሉ ላይ መዓቱም በሠራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ አጠፋቸው፥ ለመታረድም አሳልፎ ሰጣቸው።
3 ፤ ከእነርሱም የተገደሉት ይጣላሉ፥ የሬሳቸውም ግማት ይሸታል፥ ተራሮችም ከደማቸው የተነሣ ይርሳሉ።
4 ፤ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ ይበሰብሳሉ፥ ሰማያትም እንደ መጽሐፍ ጥቅልል ይጠቀለላሉ፥ ከወይንና ከበለስም ቅጠል እንደሚረግፍ ሠራዊታቸው ሁሉ ይረግፋል።
5 ፤ ሰይፌ በሰማይ ሆና እስክትረካ ድረስ ጠጥታለች፤ እነሆ፥ በኤዶምያስና በረገምሁት ሕዝብ ላይ ለፍርድ ትወርዳለች።
6 ፤ እግዚአብሔር መሥዋዕት በባሶራ፥ ታላቅም እርድ በኤዶምያስ ምድር አለውና የእግዚአብሔር ሰይፍ በደም ተሞልታለች፥ በስብም፥ በበግ ጠቦትና በፍየል ደምም፥ በአውራም በግ ኵላሊት ስብ ወፍራለች።
7 ፤ ጎሽ ከእነርሱ ጋር፥ ወይፈኖችም ከኮርማዎች ጋር ይወድቃሉ፤ ምድራቸውም በደም ትረካለች፥ አፈራቸውም በስብ ትወፍራለች።
8 ፤ የእግዚአብሔር የበቀሉ ቀን፥ ስለ ጽዮንም ክርክር የብድራት ዓመት ነው።
9 ፤ የኤዶምያስም ፈሳሾች ዝፍት ሆነው ይለወጣሉ፥ አፈርዋም ዲን ይሆናል፥ መሬትዋም የሚቀጠል ዝፍት ትሆናለች።
10 ፤ በሌሊትና በቀንም አትጠፋም፥ ጢስዋም ለዘላለም ይወጣል፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም ድረስ ባድማ ሆና ትኖራለች፤ ለዘላለም ዓለም ማንም አያልፍባትም።
11 ፤ ጭልፊትና ጃርት ግን ይወርሱአታል፤ ጕጕትና ቍራም ይኖሩባታል፤ በላይዋም የመፍረስ ገመድና የባዶነት ቱንቢ ይዘረጋባታል።
12 ፤ መሳፍንቶችዋን ወደ መንግሥት ይጠራሉ፥ ነገር ግን ማንም አይገኝባትም፤ አለቆችዋም ሁሉ ምናምኖች ይሆናሉ።
13 ፤ በአዳራሾችዋም እሾህ በቅጥሮችዋም ሳማን አሜከላ ይበቅሉባታል፤ የቀበሮም ማደሪያና የሰጐን ስፍራ ትሆናለች።
14 ፤ የምድረ በዳም አራዊት ከተኵሎች ጋር ይገናኛሉ፥ አጋንንትም እርስ በርሳቸው ይጠራራሉ፤ ጅንም በዚያ ትኖራለች ለእርስዋም ማረፊያ ታገኛለች።
15 ፤ በዚያም ዋሊያ ቤትዋን ትሠራለች እንቍላልም ትጥላለች ትቀፈቅፈውማለች ልጆችዋንም በጥላዋ ትሰበስባለች፤ በዚያም ደግሞ አሞራዎች እያንዳንዳቸው ከባልንጀሮቻቸው ጋር ይሰበሰባሉ።
16 ፤ በእግዚአብሔር መጽሐፍ ፈልጉ አንብቡም፤ አፌ አዝዞአልና፥ መንፈሱም ሰብስቦአቸዋልና ከእነዚህ አንዲት አትጠፋም፥ ባልንጀራውንም የሚያጣ የለም።
17 ፤ እርሱም ዕጣ ጣለባቸው፥ እጁም በገመድ ከፈለችላቸው፤ ለዘላለም ይገዙአታል፥ ከትውልድም እስከ ትውልድ ድረስ ይቀመጡባታል።