ምዕራፍ 27

በዚያም ቀን እግዚአብሔር ፈጣኑን እባብ ሌዋታንን ጠማማውንም እባብ ሌዋታንን በጠንካራ በታላቅም በብርቱም ሰይፍ ይቀጣል፥ በባሕርም ውስጥ ያለውን ዘንዶ ይገድላል።
2 ፤ በዚያም ቀን ለተወደደው የወይን ቦታ ተቀኙለት።
3 ፤ እኔ እግዚአብሔር ጠባቂው ነኝ፤ ሁልጊዜ አጠጣዋለሁ፤ ማንም እንዳይጐዳው በሌሊትና በቀን እጠብቀዋለሁ።
4 ፤ አልቈጣም፤ እሾህና ኵርንችት በእኔ ላይ ምነው በሰልፍ በነበሩ! በእነርሱ ላይ ተራምጄ በአንድነት ባቃጠልኋቸው ነበር።
5 ፤ ወይም ጕልበቴን ይያዝ፥ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ፤ ከእኔ ጋር ሰላም ያድርግ።
6 ፤ በሚመጣው ዘመን ያዕቆብ ሥር ይሰድዳል፥ እስራኤልም ያብባል ይጨበጭብማል፤ በፍሬያቸውም የዓለሙን ፊት ይሞላሉ።
7 ፤ በውኑ የመቱትን እንደ መታ እንዲሁ እርሱን መታውን? ወይስ እነርሱ እንደ ተገደሉበት መገደል እርሱ ተገድሎአልን?
8 ፤ ነዳቸው ሰደዳቸው ቀሠፋቸው፤ የምሥራቅ ነፋስ እንደሚነፍስበት ቀን በጠንካራ ዐውሎ አስወገዳቸው።
9 ፤ ስለዚህም የማምለኪያ ዐፀዶችና የፀሐይ ምስሎች ዳግመኛ እንዳይነሡ የመሠዊያውን ድንጋይ ሁሉ እንደ ደቀቀ እንደ ኖራ ድንጋይ ባደረገ ጊዜ፥ እንዲሁ የያዕቆብ በደል ይሰረያል፥ ይህም ኀጢአትን የማስወገድ ፍሬ ሁሉ ነው።
10 ፤ የተመሸገችው ከተማ ብቻዋን ሆነች፤ እንደ ምድረ በዳ ሆና የተፈታችና የተተወች መኖሪያ ናት፤ በዚያም ጥጃ ይሰማራል በዚያም ይተኛል ቅርንጫፍዋንም ይበላል።
11 ፤ ጫፎችዋ በደረቁ ጊዜ ይሰበራሉ፥ ሴቶችም መጥተው ያቃጥሉአቸዋል፤ የማያስተውል ሕዝብ ነውና ስለዚህ ፈጣሪው አይራራለትም ሠሪውም ምሕረት አያደርግለትም።
12 ፤ በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከወንዝ ፈሳሽ ጀምሮ እስከ ግብጽ ወንዝ ድረስ እህሉን ይወቃል፥ እናንተም የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አንድ በአንድ ትሰበሰባላችሁ።
13 ፤ በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ታላቅ መለከት ይነፋል፥ በአሦርም የጠፉ፥ በግብጽ ምድርም የተሰደዱ ይመጣሉ፥ በተቀደሰውም ተራራ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ይሰግዳሉ።