ምዕራፍ 1

ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፤ ሰው ሁሉ ከቤተ ሰቡ ጋር ገባ።
2 ፤ ሮቤል፥
3 ፤ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፥
4 ፤ ብንያም፥ ዳን፥ ንፍታሌም፥ ጋድ፥ አሴር።
5 ፤ ከያቆብ ጕልበት የወጡት ሰዎች ሁሉ ሰባ ነፍሶች ነበሩ፤ ዮሴፍም አስቀድሞ በግብፅ ነበረ።
6 ፤ ዮሴፍም ሞተ፥ ወንድሞቹም፥ ያም ትውልድ ሁሉ።
7 ፤ የእስራኤልም ልጆች አፈሩ፥ እጅግም በዙ፥ ተባዙም፥ አጅግም ጸኑ፤ ምድሪቱም በእነርሱ ሞላች።
8 ፤ በግብፅም ዮሴፍን ያላወቀ አዲስ ንጉሥ ተነሣ።
9 ፤ እርሱም ሕዝቡን። እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ሕዝብ ከእኛ ይልቅ በዝተዋል በርትተውማል፤
10 ፤ እንዳይበዙ፥ ሰልፍም በተነሳብን ጊዜ ጠላቶቻችንን አግዘው እንዳይወጉን ከምድሪቱም እንዳይወጡ፥ ኑ እንጠበብባቸው አለ።
11 ፤ በብርቱ ሥራም ያስጨንቁአቸው ዘንድ ግብር አስገባሪዎችን ሾመባቸው፤ ለፈርዖንም ፊቶምንና ራምሴን ጽኑ ከተሞች አድርገው ሠሩ።
12 ፤ ነገር ግን እንዳስጨነቁአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፥ እጅግም ጸኑ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ተጸይፈዋቸው ነበር።
13 ፤ ግብፃውያንም የእስራኤልን ልጆች በመከራ ገዙአቸው።
14 ፤ በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ፥ በጡብም በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፥ ሕይወታቸውን ያስመርሩአቸው ነበር።
15 ፤ የግብፅም ንጉሥ አንዲቱ ሲፓራ ሁለተኛይቱም ፉሐ የሚባሉትን የዕብራውያንን አዋላጆች እንዲህ ብሎ ተናገረ።
16 ፤ እናንተ የዕብራውያንን ሴቶች ስታዋልዱ፥ ለመውለድ እንደደረሱ ባያችሁ ጊዜ፥ ወንድ ቢሆን ግደሉት፤ ሴት ብትሆን ግን በሕይወት ትኑር።
17 ፤ አዋላጆች ግን እግዚአብሔርን ፈሩ፥ የግብፅ ንጉሥም እንዳዘዛቸው አላደረጉም፥ ወንዶቹን ሕፃናትንም አዳኑአቸው።
18 ፤ የግብፅም ንጉሥ አዋላጆችን ጠርቶ። ለምን እንዲህ አደረጋችሁ? ወንዶቹን ሕፃናትንስ ለምን አዳናችሁ? አላቸው።
19 ፤ አዋላጆቹም ፈርዖንን። የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብፅ ሴቶች ስላልሆኑ፤ እነርሱ ጠንካሮች ናቸውና አዋላጆች ሳይገቡ ስለሚወልዱ ነው አሉት።
20 ፤ እግዚአብሔርም ለአዋላጆች መልካም አደረገላቸው፤ ሕዝቡም በዛ፥ እጅግም ጸና።
21 ፤ እንዲህም ሆነ፤ አዋላጆች እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ ቤቶችን አደረገላቸው።
22 ፤ ፈርዖንም። የሚወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ ወደ ወንዝ ጣሉት፥ ሴትን ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት አድኑአት ብሎ ሕዝቡን ሁሉ አዘዘ።