ምዕራፍ 13

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገርው።
2 ፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንስሳም ማሕፀንን የሚከፈት በኵር ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ የእኔ ነው።
3 ፤ ሙሴም ሕዝቡን አለ። ከባርነት ቤት ከግብፅ የወጣችሁበትን ይህን ቀን አስቡ፥ እግዚአብሔር ከዚህ ቦታ በብርቱ እጅ አውጥቶአችኋልና፤ ስለዚህ የቦካ እንጀራ አትብሉ።
4 ፤ እናንተ ዛሬ በአቢብ ወር ወጥታችኋል።
5 ፤ እግዚአብሔርም ለአንተ ይሰጣት ዘንድ ለአባቶችህ ወደ ማለላቸው፥ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር፥ ወደ ከነዓናውያን ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ምድር ባገባህ ጊዜ ይህችን አምልኮ በዚህ ወር ታደርጋለህ።
6 ፤ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ለእግዚአብሔር በዓል ይሆናል።
7 ፤ ሰባት ቀንም ሙሉ ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፥ በአንተም ዘንድ እርሾ ያለበት እንጀራ አይታይ፥ በድንበርህም ሁሉ እርሾ አይታይ።
8 ፤ በዚያም ቀን። ከግብፅ በወጣሁ ጊዜ እግዚአብሔር ስላደረገልኝ ነው ስትል ለልጅህ ትነግረዋለህ።
9 ፤ እግዚአብሔር በብርቱ እጅ ከግብፅ አውጥቶሃልና የእግዚአብሔር ሕግ በአፍህ ይሆን ዘንድ በእጅህ እንደ ምልክት በዓይኖችህም መካከል እንደ መታሰቢያ ይሁንልህ።
10 ፤ በዓመት በዓመት በወራቱ ይህችን ሥርዓት ጠብቃት።
11 ፤ እግዚአብሔርም ለአንተ ለአባቶችህም እንደ ማለ ወደ ከነዓናውያን ምድር ባገባህ ጊዜ፥ እርስዋንም በሰጠህ ጊዜ፥
12 ፤ ማሕፀንን የሚከፍተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ለይ፤ ከሚሆንልህ ከብት ሁሉ ተባት ሆኖ አስቀድሞ የተወለደው ለእግዚአብሔር ይሆናል።
13 ፤ የአህያውን በኵር በጠቦት ትዋጀዋለህ፥ ባትዋጀውም አንገቱን ትሰብረዋለህ፤ የሰውንም በኵር ሁሉ ከልጆችህ መካከል ትዋጀዋለህ።
14 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ በሚመጣው ጊዜ ልጅህ። ይህ ምንድር ነው? ብሎ በጠየቀህ ጊዜ እንዲህ ትለዋለህ። እግዚአብሔር በብርቱ እጅ ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር አወጣን፤
15 ፤ ፈርዖንም እንዳይሰድደን ልቡን ባጸና ጊዜ እግዚአብሔር ከሰው በኵር ጀምሮ እስከ እንስሳ በኵር ድረስ በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ ገደለ፤ ስለዚህ ወንድ ሆኖ ማሕፀንን የከፈተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሠዋለሁ፥ ነገር ግን የልጆቼን በኵር ሁሉ እዋጃለሁ።
16 ፤ እግዚአብሔርም በብርቱ እጅ ከግብፅ አውጥቶናልና በእጅህ እንደ ምልክት፥ በዓይኖችህም መካከል እንደ ተንጠለጠለ ነገር ይሁንልህ።
17 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ፥ ምንም ቅርብ ቢሆን እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ምድር መንገድ አልመራቸውም፤ እግዚአብሔር። ሕዝቡ ሰልፉን ባየ ጊዜ እንዳይጸጽተው ወደ ግብፅም እንዳይመለስ ብሎአልና።
18 ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን በዙሪያ መንገድ በኤርትራ ባሕር ባለችው ምድረ በዳ መራቸው። የእስራኤልም ልጆች ከግብፅ ምድር ተሰልፈው ወጡ።
19 ፤ ዮሴፍም። እግዚአብሔር ሳይጎበኛችሁ አይቀርም፥ አጥንቶቼንም ከዚህ ከእናንተ ጋር ታወጣላችሁ ብሎ የእስራኤልን ልጆች አምሎአቸው ነበርና ሙሴ የእርሱን አጥንቶች ከእርሱ ጋር ወሰደ።
20 ፤ ከሱኮትም ተጓዙ፥ በምድረ በዳውም ዳር በኤታም ሰፈሩ።
21 ፤ በቀንና በሌሊትም ይሄዱ ዘንድ፥ መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሊያበራላቸውም ሌሊት በእሳት ዓምድ እግዚአብሔር በፊታቸው ሄደ።
22 ፤ የደመና ዓምድ በቀን፥ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከሕዝቡ ፊት ከቶ ፈቀቅ አላለም።