ምዕራፍ 6

እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። በጸናች እጅ ይለቅቃችኋልና፥ በጸናችም እጅ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋልና አሁን በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ።
2 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤
3 ፤ ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር።
4 ፤ የተሰደዱባትንም ምድር፥ የእንግድነታቸውን የከነዓንን ምድር፥ እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን አቆምሁ።
5 ፤ ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ።
6 ፤ ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከግብፃውያንም ባርነት አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፥
7 ፤ ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።
8 ፤ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁባት ምድር አገባችኋለሁ፤ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
9 ፤ ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከሰውነታቸው መጨነቅ ከከባዱም ሥራ የተነሣ ቃሉን አልሰሙትም።
10 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
11 ፤ ግባ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ ይለቅቅ ዘንድ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር።
12 ፤ ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት። እነሆ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? ይልቁንም እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ ብሎ ተናገረ።
13 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ተናገራቸው፥ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ እንዲያወጣቸው ይነግሩት ዘንድ አዘዛቸው።
14 ፤ የአባታቸውም ቤት አለቆች እነዚህ ናቸው። የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉስ፥ አስሮን፥ ከርሚ፤ እነዚህ የሮቤል ወገኖች ናቸው።
15 ፤ የስምዖንም ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ዶሐር፥ የከነዓናዊቱም ልጅ ሳኡል፤ እነዚህ የስምዖን ወገኖች ናቸው።
16 ፤ እነዚህም እንደ ወገኖቻቸው የሌዊ ልጆች ስሞች ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ ናቸው። የሌዊም የሕይወት ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው።
17 ፤ የጌድሶንም ልጆች እንደ ወገኖቻቸው ሎቤኒ፥ ሰሜኢ ናቸው።
18 ፤ የቀዓትም ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል ናቸው፤ የቀዓትም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነው።
19 ፤ የሜራሪ ልጆች ሞሖሊ፥ ሙሲ ናቸው። እነዚህ እንደ ትውልዳቸው የሌዊ ወገኖች ናቸው።
20 ፤ እንበረምም የአጎቱን ልጅ ዮካብድን አገባ፥ አሮንና ሙሴንም ወለደችለት፤ የእንበረምም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው።
21 ፤ የይስዓር ልጆች ቆሬ፥ ናፌግ፥ ዝክሪ ናቸው።
22 ፤ የዑዝኤል ልጆች ሚሳኤል፥ ኤልዳፋን፥ ሥትሪ ናቸው።
23 ፤ አሮንም የአሚናዳብን የነአሶንን እኅት ኤልሳቤጥን አገባ፥ እርስዋም ናዳብንና አብዮድን አልዓዛርንና ኢታምርን ወለደችለት።
24 ፤ የቆሬ ልጆች አሴር፥ ሕልቃና፥ አብያሳፍ ናቸው፤ እነዚህ የቆሬ ልጆች ወገኖች ናቸው።
25 ፤ የአሮንም ልጅ አልዓዛር ከፉትኤል ልጆች ሚስት አገባ፥ እርስዋም ፊንሐስን ወለደችለት። እነዚህ እንደ ወገኖቻቸው የሌዋውያን አባቶች አለቆች ናቸው።
26 ፤ እነዚህ አሮንና ሙሴ እግዚአብሔር። ከግብፅ ምድር በየሠራዊቶቻቸው የእስራኤልን ልጆች አውጡ ያላቸው ናቸው።
27 ፤ እነዚህ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ያወጡ ዘንድ ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር የተነጋገሩ ናቸው፤ እነዚህ ሙሴና አሮን ናቸው።
28 ፤ እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ሙሴን በተናገረው ቀን እንዲህ ሆነ፤
29 ፤ እግዚአብሔር ሙሴን። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እኔ የምነግርህን ሁሉ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር ብሎ ተናገረው።
30 ፤ ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት። እነሆ እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? አለ።