ምዕራፍ 32

ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው። ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት።
2 ፤ አሮንም። በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ አላቸው።
3 ፤ ሕዝቡም ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት።
4 ፤ ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አላቸው።
5 ፤ አሮንም ባየው ጊዜ መሠዊያን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም።ነገ የእግዚአብሔር በዓል ነው ሲል አወጀ።
6 ፤ በነጋውም ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፥ የደኅነትም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ሊዘፍኑም ተነሡ።
7 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ከግብፅ ምድር ያወጣኸው ሕዝብህ ኃጢአት ሠርተዋልና ሂድ፥ ውረድ።
8 ፤ ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አደረጉ፥ ሰገዱለትም፥ ሠዉለትም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አሉ ሲል ተናገረው።
9 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው።
10 ፤ አሁንም ቍጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው።
11 ፤ ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፥ አለም። አቤቱ፥ ቍጣህ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ስለ ምን ተቃጠለ?
12 ፤ ግብፃውያንስ። በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ።
13 ፤ ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ።
14 ፤ እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ።
15 ፤ ሙሴም ተመለሰ፥ ሁለቱንም የምስክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር።
16 ፤ ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቶች ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ።
17 ፤ ኢያሱም እልል ሲሉ የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ሙሴን። የሰልፍ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ አለ አለው።
18 ፤ እርሱም። ይህ የድል ነሺዎች ወይም የድል ተነሺዎች ድምፅ አይደለም፥ ነገር ግን የዘፈን ድምፅ እሰማለሁ አለው።
19 ፤ እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንም ዘፈኑንም አየ፤ የሙሴም ቍጣ ተቃጠለ፥ ጽላቶቹንም ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰበራቸው።
20 ፤ የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፥ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጨው፥ በውኃውም ላይ በተነው፥ ለእስራኤልም ልጆች አጠጣው።
21 ፤ ሙሴም አሮንን። ይህን ታላቅ ኃጢአት ታመጣበት ዘንድ ይህ ሕዝብ ምን አደረገህ? አለው።
22 ፤ አሮንም እንዲህ አለ። ጌታዬ ሆይ፥ ቍጣህ አይቃጠል፤ ይህ ሕዝብ ክፋትን እንዲወድድ አንተ ታውቃለህ።
23 ፤ እነርሱም። ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉኝ።
24 ፤ እኔም። ከእናንተ ወርቅ ያለው ሰው ከእርሱ ሰብሮ ያምጣልኝ አልኋቸው፤ ሰጡኝም፤ በእሳትም ላይ ጣልሁት፥ ይህም ጥጃ ወጣ።
25 ፤ ሙሴም በጠላቶቻቸው ፊት እንዲነወሩ አሮን ስድ ለቅቋቸዋልና ሕዝቡ ስድ እንደ ተለቀቁ ባየ ጊዜ፥
26 ፤ በሰፈሩ ደጅ ቆሞ። የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ! አለ፤ የሌዊም ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ።
27 ፤ እርሱም። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእናንተ ሰው ሁሉ ሰይፉን በወገቡ ላይ ይታጠቅ፥ በሰፈሩም ውስጥ በዚህና በዚያ ከበር እስከ በር ተመላለሱ፥ የእናንተም ሰው ሁሉ ወንድሙን ወዳጁንም ጎረቤቱንም ይግደል አላቸው።
28 ፤ የሌዊም ልጆች ሙሴ እንዳለ አደረጉ፤ በዚያም ቀን ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ሰዎች ሞቱ።
29 ፤ ሙሴም። ዛሬ በረከትን እንዲያወርድላችሁ እያንዳንዳችሁ በልጃችሁና በወንድማችሁ ላይ ዛሬ እጃችሁን ለእግዚአብሔር ቅዱስ አድርጉ አለ።
30 ፤ በነጋውም ሙሴ ለሕዝቡ። እናንተ ታላቅ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ አሁንም ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤ ምናልባት ኃጢአታችሁን አስተሰርይላችኋለሁ አላቸው።
31 ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ። ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤
32 ፤ አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለ።
33 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የበደለኝን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ።
34 ፤ አሁንም ሂድ፥ ይህንም ሕዝብ ወደ ነገርሁህ ምራ፤ እነሆ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኃጢአታቸውን አመጣባቸዋለሁ አለው።
35 ፤ አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ቀሠፈ።