ምዕራፍ 31

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ እይ ከይሁዳ ነገድ የሚሆን የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠርቼዋለሁ።
3 ፤ በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእዚአብሔርን መንፈስ ሞላሁበት፤
4 ፤ የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሰራ ዘንድ፥
5 ፤ ለፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ።
6 ፤ እኔም እነሆ ከእርሱ ጋር ከዳን ነገድ የሚሆን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን ሰጠሁ፤ ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ጥበበኞች በሆኑት ሁሉ ጥበብን አኖርሁ።
7 ፤ የመገናኛውን ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥ በእርሱም ላይ ያለውን የስርየት መክደኛውን፥ የድንኳኑንም ዕቃ ሁሉ፥
8 ፤ ገበታውንም ዕቃውንም፥ ከዕቃው ሁሉ ጋር የነጻውን መቅረዝ፥ የዕጣን መሠዊያውን፥
9 ፤ ለሚቃጠል መሥዋት የሚሆነውንም መሠዊያ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፥ በብልሃት የተሠራውንም ልብስ፥
10 ፤ በክህነት እኔን የሚያገለግሉበትን የካህኑን የአሮንን ልብሰ ተክህኖና የልጆቹን ልብስ፥
11 ፤ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ለመቅደሱ የሚሆን የጣፋጭ ሽቱውንም ዕጣን እንዳዘዝሁህ ሁሉ ያድርጉ።
12 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።
13 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ ምልክት ነውና ሰንበቶቼን ፈጽሞ ጠብቁ።
14 ፤ ስለዚህ ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን ጠብቁ፤ የሚያረክሰውም ሰው ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፥ ሥራንም በእርሱ የሠራ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ።
15 ፤ ስድስት ቀን ሥራን ሥራ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል።
16 ፤ የእስራኤልም ልጆች ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ቃል ኪዳን በሰንበት ያርፉ ዘንድ ሰንበትን ይጠብቁ።
17 ፤ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ስለ ፈጠረ፥ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው ስላረፈና ስለ ተነፈሰ፥ በእኔና በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ምልክት ነው።
18 ፤ እግዚአብሔርም ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ከድንጋይ የሆኑ ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ሰጠው።