ምዕራፍ 15

በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።
2 ፤ ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ።
3 ፤ እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው፥
4 ፤ የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት ሦስተኞች በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ።
5 ፤ ቀላያትም ከደኑአቸው፤ ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ።
6 ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ።
7 ፤ በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰድደህ፥ እንደ ገለባም በላቸው።
8 ፤ በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር ውስጥ ረጋ።
9 ፤ ጠላትም። አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ።
10 ፤ ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ።
11 ፤ አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?
12 ፤ ቀኝህን ዘረጋህ፥ ምድርም ዋጠቻቸው።
13 ፤ በቸርነትህ የተቤዠሃቸውን ሕዝብህን መራህ፤ በኃይልህ ወደ ቅዱስ ማደሪያህ አገባሃቸው።
14 ፤ አሕዛብ ሰሙ፥ ተንቀጠቀጡም፤ በፍልስጥኤም የሚኖሩትን ምጥ ያዛቸው።
15 ፤ የዚያን ጊዜ የኤዶም አለቆች ደነገጡ፤ የሞአብን ኃያላን መንቀጥቀጥ ያዛቸው፤ በከነዓን የሚኖሩ ሁሉ ቀለጡ።
16 ፤ አቤቱ፥ ሕዝብህ እስኪያልፍ ድረስ፥ የተቤዠኸው ሕዝብ እስኪያልፍ ድረስ፥ ፍርሃትና ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ በክንድህ ብርታት እንደ ድንጋይ ዝም አሉ።
17 ፤ አቤቱ፥ አንተ ታስገባቸዋለህ፥ በርስትህ ተራራም ትተክላቸዋለህ፥ አቤቱ፥ ለማደሪያህ ባደረግኸው ስፍራ፥ አቤቱ፥ እጆችህ ባዘጋጁት መቅደስ።
18 ፤ እግዚአብሔር ለዘላለሙ እስከ ፍጻሜ ይነግሣል።
19 ፤ የፈርዖን ፈረሶች ከሰረገሎቹ ከፈረሰኞቹም ጋር ወደ ባሕር ገቡ፥ እግዚአብሔርም የባሕሩን ውኆች መለሰባቸው፤ የእስራኤል ልጆች ግን በባሕሩ መካከል በየብስ ሄዱ።
20 ፤ የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ።
21 ፤ ማርያምም እየዘመረች መለሰችላቸው። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።
22 ፤ ሙሴም እስራኤልን ከኤርትራ ባሕር አስጓዘ፥ ወደ ሱርም ምድረ በዳ ወጡ፤ በምድረ በዳም ሦስት ቀን ሄዱ፥ ውኃም አላገኙም።
23 ፤ ወደ ማራም በመጡ ጊዜ የማራ ውኃ መራራ ነበረና ሊጠጡ አልቻሉም፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም ማራ ተብሎ ተጠራ።
24 ፤ ሕዝቡም። ምን እንጠጣለን? ብለው በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ።
25 ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፥ በውኃውም ላይ ጣለው፥ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤
26 ፤ እርሱም። አንተ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ፥ በፊቱም የሚበጀውን ብታደርግ፥ ትእዛዙንም ብታደምጥ፥ ሥርዓቱንም ሁሉ ብትጠብቅ፥ በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና አለ።
27 ፤ እነርሱም ወደ ኤሊም መጡ፥ በዚያም አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ነበሩባት፤ በዚያም በውኃው አጠገብ ሰፈሩ።