ምዕራፍ 16

ከኤሊምም ተጓዙ፥ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከግብፅ አገር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ።
2 ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አንጐራጐሩ።
3 ፤ የእስራኤልም ልጆች። ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ እኛን ወደዚች ምድረ በዳ አውጥታችኋል፤ በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እንጀራ ስንበላ ስንጠግብ ሳለን በግብፅ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን! አሉአቸው።
4 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይልቀሙ።
5 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ ዕለት ዕለትም ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን አለው።
6 ፤ ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ። እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር እንዳወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፥
7 ፤ የእግዚአብሔርንም ክብር ጥዋት ታያላችሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ያንጐራጐራችሁትን ሰምቶአልና በእኛም ላይ የምታንጐራጕሩ እኛ ምንድር ነን? አሉ።
8 ፤ ሙሴም። እግዚአብሔር ያንጐራጐራችሁበትን ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና በመሸ ጊዜ ትበሉ ዘንድ ሥጋን፥ ማልዶም ትጠግቡ ዘንድ እንጀራን እግዚአብሔር ይሰጣችኋል፤ እኛም ምንድር ነን? ማንጐራጐራችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በእኛ አይደለም አለ።
9 ፤ ሙሴም አሮንን። ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ። ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ በል አለው።
10 ፤ እንዲህም ሆነ፤ አሮን ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አቀኑ፤ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ታየ።
11
12 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። የእስራኤልን ልጆች ማንጐራጐር ሰማሁ። ወደ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፥ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው።
13 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፥ ሰፈሩንም ከደኑት፤ ማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጠል ወድቆ ነበር።
14 ፤ የወደቀውም ጠል ባለፈ ጊዜ፥ እነሆ በመሬት ላይ እንደ ደቃቅ ውርጭ ሆኖ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ ታየ።
15 ፤ የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደ ሆነ አላወቁምና እርስ በእርሳቸው። ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። ሙሴም። ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው።
16 ፤ እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይልቀም፤ በድኳኑ ባሉት ነፍሶች ቍጥር ለአንድ ሰው አንድ ጎሞር ውሰዱ አላቸው።
17 ፤ የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዱ አብዝቶ አንዱም አሳንሶ ለቀመ።
18 ፤ በጎሞርም በሰፈሩት ጊዜ እጅግ ለለቀመ አልተረፈውም ጥቂትም ለለቀመ አልጐደለበትም፤ ሁሉ እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ለቀመ።
19 ፤ ሙሴም። ማንም ከእርሱ አንዳች ለነገ አያስቀር አላቸው።
20 ፤ ነገር ግን ሙሴን አልሰሙትም፤ አንዳንድ ሰዎችም ከእርሱ ለነገ አስቀሩ፥ እርሱም ተላ ሸተተም፤ ሙሴም ተቈጣቸው።
21 ፤ ሰውም ሁሉ ዕለት ዕለት የሚበላውን ያህል በጥዋት ለቀመ፤ ፀሐይም በተኰሰ ጊዜ ቀለጠ።
22 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በስድስተኛው ቀን ሁለት እጥፍ አድርገው እያንዳንዳቸው ሁለት ጎሞር እንጀራ ለቀሙ፤ የማኀበሩም አለቆች ሁሉ መጥተው ለሙሴ ነገሩት።
23 ፤ እርሱም። እግዚአብሔር የተናገረው ይህ ነው። ነገ ዕረፍት፥ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ሰንበት ነው፤ የምትጋግሩትን ጋግሩ፥ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፥ የተረፈውን ሁሉ ለነገ እንዲጠበቅ አኑሩት አላቸው።
24 ፤ ሙሴም እንዳዘዘ ለነገ አኖሩት፤ አልሸተተም፥ ትልም አልሆነበትም።
25 ፤ ሙሴም። የእግዚአብሔር ሰንበት ዛሬ ነውና ብሉት፤ ዛሬ በሜዳ አታገኙትም።
26 ፤ ስድስት ቀን ልቀሙት፤ ሰባተኛው ቀን ግን ሰንበት ነው፤ በእርሱ አይገኝም አለ።
27 ፤ በሰባተኛውም ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሕዝቡ አንዳንድ ሰዎች ሊለቅሙ ወጡ፥ ምንምን አላገኙም።
28 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ለመጠበቅ እስከ መቼ እንቢ ትላላችሁ?
29 ፤ እግዚአብሔር ሰንበትን እንደ ሰጣችሁ እዩ፤ ስለዚህ በስድስተኛው ቀን የሁለት ቀን እንጀራ ሰጣችሁ፤ ሰው ሁሉ በስፍራው ይቀመጥ፥ በሰባተኛው ቀን ማንም ከስፍራው አይሂድ አለው።
30 ፤ ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፈ።
31 ፤ የእስራኤልም ወገን ስሙን መና ብለው ጠሩት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ ነው፤ ጣዕሙም እንደ ማር ቂጣ ነው።
32 ፤ ሙሴም። እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። ከግብፅ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ ያበላኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ ከእርሱ አንድ ጎሞር ሙሉ ለልጅ ልጆቻችሁ ይጠበቅ አለ።
33 ፤ ሙሴም አሮንን። አንድ ማድጋ ወስደህ ጎሞር ሙሉ መና አግባበት፥ ለልጅ ልጃችሁም ይጠበቅ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት አኑረው አለው።
34 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ይጠበቅ ዘንድ አሮን በምስክሩ ፊት አኖረው።
35 ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደሚኖሩባት ምድር እስኪመጡ ድረስ አርባ ዓመት መና በሉ፤ ወደ ከነዓን ምድር ድንበር እስኪመጡ ድረስ መና በሉ።
36 ፤ ጎሞርም የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል ነው።