ምዕራፍ 18

የምድያምም ካህን የሙሴ አማት ዮቶር እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እስራኤልን ከግብፅ እንዳወጣ ሰማ።
2 ፤ በዚያን ጊዜ የሙሴ አማት ዮቶር መልሶአት የነበረውን የሙሴን ሚስት ሲፓራን ሁለቱንም ልጆቿን ወሰደ።
3 ፤ ከእነርሱ የአንደኛው ስም ጌርሳም ነበረ፤ አባቱ። በሌላ አገር ስደተኛ ነበርሁ ብሎአልና፤
4 ፤ የሁለተኛውም ስም አልዓዛር ነበረ። የአባቴ አምላክ ረዳኝ፥ ከፈርዖንም ሰይፍ አዳነኝ ብሎአልና።
5 ፤ የሙሴ አማት ዮቶርም ከልጆቹና ከሚስቱ ጋር በእግዚአብሔር ተራራ አጠገብ በምድረ በዳ ወደ ሰፈረ ወደ ሙሴ መጣ።
6 ፤ ሙሴንም። እኔ አማትህ ዮቶር፥ ሚስትህም፥ ከእርስዋም ጋር ሁለቱ ልጆችዋ መጥተንልሃል አለው።
7 ፤ ሙሴም አማቱን ሊገናኝ ወጣ፥ ሰገደም፥ ሳመውም፤ እርስ በርሳቸውም ደኅንነታቸውን ተጠያየቁ፥ ወደ ድንኳኑም ገቡ።
8 ፤ ሙሴም እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፃውያን ላይ ስለ እስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ በመንገድም ያገኛቸውን ድካም ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እንዳዳናቸው ለአማቱ ነገረው።
9 ፤ ዮቶርም እግዚአብሔር ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ሁሉ፥ ከግብፃውያንም እጅ ስላዳናቸው ደስ አለው።
10 ፤ ዮቶርም። ከግብፃውያንና ከፈርዖን እጅ ያዳናችሁ፥ ከግብፃውያንም እጅ ሕዝቡን ያዳነ እግዚአብሔር ይባረክ።
11 ፤ ትዕቢት ባደረጉባቸው ነገር እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አሁን አወቅሁ አለ።
12 ፤ የሙሴ አማት ዮቶርም የሚቃጠል መሥዋዕትንና ሌላ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ወሰደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከሙሴ አማት ጋር እንጀራ ሊበሉ አሮን የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ።
13 ፤ እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ በሕዝቡ ሊፈርድ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በሙሴ ፊት ከጥዋት እስከ ማታ ድረስ ቆመው ነበር።
14 ፤ የሙሴም አማት በሕዝቡ ያደረገውን ሁሉ ባየ ጊዜ። ይህ በሕዝቡ የምታደርገው ምንድር ነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በዙሪያህ ቆመው ሳሉ አንተ ብቻህን ስለ ምን ተቀምጠሃል? አለው።
15 ፤ ሙሴም አማቱን። ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤
16 ፤ ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፥ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ አለው።
17 ፤ የሙሴም አማት አለው። አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም።
18 ፤ ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም።
19 ፤ አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፥ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፤
20 ፤ ሥርዓቱንም ሕጉንም አስተምራቸው፥ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያደርጉትንም ሥራ ሁሉ አሳያቸው።
21 ፤ አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ የታመኑ፥ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ፤ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የአሥርም አለቆችን ሹምላቸው።
22 ፤ በሕዝቡ ላይ ሁልጊዜ ይፍረዱ፤ አውራውን ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት፥ ታናሹንም ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ፤ እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ፥ ለአንተም ይቀልልልሃል።
23 ፤ ይህንም ብታደርግ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ፥ መቆም ይቻልሃል፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል።
24 ፤ ሙሴም የአማቱን ቃል ሰማ፥ ያለውንም ሁሉ አደረገ።
25 ፤ ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ አዋቂዎችን መረጠ፥ በሕዝቡም ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶም አለቆች፥ የአምሳም አለቆች፥ የአሥርም አለቆች አድርጎ ሾማቸው።
26 ፤ በሕዝቡም ላይ ሁልጊዜ ፈረዱ፤ የከበደባቸውንም ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፥ ታናሹን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ።
27 ፤ ሙሴም አማቱን ሰደደው፤ እርሱም ወደ አገሩ ተመለሰ።