ምዕራፍ 38

ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆን መሠዊያን ከግራር እንጨት አደረገ፤ አራት ማዕዘንም ነበረ፤ ከፍታው ሦስት ክንድ ነበረ።
2 ፤ ቀንዶቹንም በአራቱ ማዕዘን አደረገበት፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ነበሩ፤ በናስም ለበጠው።
3 ፤ የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥ ምንቸቶቹንም፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አደረገ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አደረገ።
4 ፤ እንደ መረብ ሆኖም የተሠራ የናስ መከታ ለመሠዊያ አደረገ፤ መከታውም እስከ መሠዊያው እኩሌታ ይደርስ ዘንድ በመሠዊያው በሚዞረው በደረጃው ታች አደረገው።
5 ፤ ለናሱም መከታ ለአራቱ ማዕዘን የመሎጊያዎች ስፍራ ይሆኑ ዘንድ አራት ቀለበቶች አደረገ።
6 ፤ መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠራ፥ በናስም ለበጣቸው።
7 ፤ ይሸከሙትም ዘንድ በመሠዊያ ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ መሎጊያዎቹን አገባ፤ ከሳንቆቹም ሠርቶ ባዶ አደረገው።
8 ፤ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ከሴቶች መስተዋት ከናስ አደረገ።
9 ፤ አደባባዩንም አደረገ፤ በደቡብ ወገን ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ፥ የተፈተለ የጥሩ በፍታ መጋረጆች ነበሩ።
10 ፤ ከናስ የተሠሩ ሀያውን ምሰሶችና ሀያውን እግሮች አደረገ፤ የምሰሶቹንም ኩላቦችና ዘንጎች ከብር አደረገ።
11 ፤ በሰሜኑም ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች፥ ከናስም የተሠራ ሀያ ምሰሶችንና ሀያ እግሮችን፥ ለምሰሶቹም የብር ኩላቦችንና ዘንጎችን አደረገ።
12 ፤ በምዕራብም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች፥ አሥሩንም ምሰሶች፥ አሥሩንም የናስ እግሮች፥ ለምሰሶቹም የብር ኩላቦችንና ዘንጎችን አደረገ።
13 ፤ በምሥራቅም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች አደረገ።
14 ፤ በአንድ ወገንም የመጋረጆቹ ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ፥ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ነበሩ።
15 ፤ እንዲሁም በሁለተኛው ወገን በአደባባዩ ደጅ በዚህና በዚያ አሥራ አምስት ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ ሦስትም ምሰሶች፥ ሦስትም እግሮች ነበሩ።
16 ፤ በአደባባዩ ዙሪያ ያሉ መጋረጆች ሁሉ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ተሠርተው ነበር።
17 ፤ የምሰሶቹም እግሮች የናስ፥ የምሰሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ነበሩ፤ የምሰሶችም ጕልላቶች በብር ተለብጠው ነበር፤ በአደባባዩ ላሉ ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች ነበሩአቸው።
18 ፤ የአደባባዩም ደጅ መጋረጃ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ፥ ከጥሩም በፍታ በጥልፍ አሠራር የተሠራ ነበረ፤ ርዝመቱ ሀያ ክንድ ነበረ፥ ቁመቱም እንደ አደባባዩ መጋረጆች አምስት ክንድ ነበረ፤
19 ፤ ከናስ የተሠሩ ምሰሶቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ነበሩ፤ ኩላቦቹ የብር ነበሩ፤ ጕልላቶቹና ዘንጎቹም በብር ተለብጠው ነበር።
20 ፤ የማደሪያውም ካስማዎች በዙሪያውም ያለ የአደባባዩ ካስማዎች የናስ ነበሩ።
21 ፤ በሙሴ ትእዛዝ ለሌዋውያን ማገልገል ሊሆን በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር እጅ እንደ ተቈጠረው የማደሪያው፥ የምስክሩ ማደሪያ፥ ዕቃ ድምር ይህ ነው።
22 ፤ ከይሁዳ ነገድም የሆነ የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤል እግዚአብሔር ለሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።
23 ፤ ከእርሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነ የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ ነበረ፤ እርሱም የቅርጽ ሠራተኛና ብልህ ሠራተኛ፥ በሰማያዊ በሐምራዊም በቀይም ግምጃ፥ በጥሩም በፍታ የሚሠራ ጠላፊ ነበረ።
24 ፤ የተሰጠው ወርቅ ሁሉ፥ በመቅደሱ ሥራ ሁሉ የተደረገው ወርቅ፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሀያ ዘጠኝ መክሊት ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል ነበረ።
25 ፤ በማኅበሩም ከሚቈጠሩት የተገኘ ብር፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ መቶ መክሊትና አንድ ሺህ ሰባት መቶ ከሰባ አምስት ሰቅል ነበረ።
26 ፤ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የሰቅል ግማሽ ከተቈጠረው ከእያንዳንዱ ሰው የተሰጠ ነው፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ሰዎች ነበሩ።
27 ፤ መቶውም የብር መክሊት የመቅደሱንና የመጋረጃውን እግሮች ለመሥራት ነበረ፤ ከመቶውም መክሊት መቶ እግሮች አደረገ፤ ለአንድ እግርም አንድ መክሊት ነበረ።
28 ፤ ከሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ሰቅል የምሰሶቹን ኩላቦችና ዘንጎች አደረገ፥ የምሰሶቹንም ጕልላቶች ለበጠ።
29 ፤ የተሰጠውም ናስ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ።
30 ፤ ከእርሱም የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ እግሮች፥ የናሱንም መሠዊያ፥ ለእርሱም የሆነውን የናሱን መከታ፥ የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥
31 ፤ በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን እግሮች፥ የአደባባዩንም ደጃፍ እግሮች፥ የማደሪያውንም ካስማዎች ሁሉ በአደባባዩ ዙሪያም ያሉትን ካስማዎች ሁሉ አደረገ።