ምዕራፍ 26

ደግሞም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ የተሠሩ አሥር መጋረጆች ያሉበትን ማደሪያ ሥራ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእነርሱ ላይ ይሁኑ።
2 ፤ የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን፤ የመጋረጆቹ ሁሉ መጠን ትክክል ይሁን።
3 ፤ አምስቱ መጋረጆች እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ፤ አምስቱም መጋረጆች እንዲሁ እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ።
4 ፤ ከሚጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አድርግ።
5 ፤ አምሳ ቀለበቶችን በአንድ መጋረጃ አድርግ፥ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አድርግ፤ ቀለበቶቹ ሁሉ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት ይሆናሉ።
6 ፤ አምሳ የወርቅ መያዣዎች ሥራ፤ ማደሪያውንም አንድ እንዲሆን መጋረጆችን እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጥማቸው።
7 ፤ ከማደሪያውም በላይ ለድንኳን የሚሆኑ መጋረጆች ከፍየል ጠጕር አድርግ፤ አሥራ አንድ መጋረጆች ታደርጋለህ።
8 ፤ እያንዳንዱም መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ እያንዳንዱም መጋረጃ ወርዱ አራት ክንድ ይሁን፤ የአሥራ አንዱም መጋረጆች መጠናቸው ትክክል ይሁን።
9 ፤ አምስቱ መጋረጆች አንድ ሆነው ይጋጠሙ፥ ስድስቱም መጋረጆች እርስ በርሳቸው አንድ ሆነው ይጋጠሙ፤ ስድስተኛውም መጋረጃ በድንኳኑ ፊት ይደረብ።
10 ፤ ከተጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንድኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አምሳ ቀለበቶች አድርግ።
11 ፤ አምሳም የናስ መያዣዎችን ሥራ፥ መያዣዎችንም ወደ ቀለበቶች አግባቸው፥ ድንኳኑም አንድ እንዲሆን አጋጥመው።
12 ፤ ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ በማደሪያው ጀርባ ይንጠልጠል።
13 ፤ ማደሪያውን እንዲሸፍን ከርዝመቱ በአንድ ወገን አንድ ክንድ፥ በአንድ ወገንም አንድ ክንድ ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረው ትርፍ በማደሪያው ውጭ በወዲህና በወዲያ ይንጠልጠል።
14 ፤ ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአቆስጣ ቁርበት አድርግ።
15 ፤ ለማደሪያውም የሚቆሙትን ሳንቆች ከግራር እንጨት አድርግ።
16 ፤ የሳንቃው ሁሉ ርዝመቱ አሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን።
17 ፤ ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ይሁኑለት፤ ለማደሪያው ሳንቆች ሁሉ እንዲሁ አድርግ።
18 ፤ ለማደሪያውም በደቡብ ወገን ሀያ ሳንቆችን አድርግ።
19 ፤ ከሀያውም ሳንቆች በታች አርባ የብር እግሮችን አድርግ፤ ከእያንዳንዱ ሳንቃ በታች ለሁለት ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ይሁኑ።
20 ፤ ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሀያ ሳንቆች፥
21 ፤ ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሁኑ።
22 ፤ ለማደሪያውም በምዕራቡ ወገን በስተ ኋላ ስድስት ሳንቆችን አድርግ።
23 ፤ ለማደሪያውም ለሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቆችን አድርግ።
24 ፤ ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንዱ ሳንቃ ድርብ ይሁን፤ እንዲሁም ለሁለቱ ይሁን፤ እነርሱም ለሁለቱ ማዕዘን ይሆናሉ።
25 ፤ ስምንት ሳንቆችና አሥራ ስድስት የብር እግሮቻቸው ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሆናሉ።
26 ፤ ከግራርም እንጨት በማደሪያው በአንድ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥
27 ፤ በማደሪያውም በሁለተኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ በማደሪያውም በስተ ኋላ በምዕራብ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች አድርግ።
28 ፤ መካከለኛውም መወርወሪያ በሳንቆች መካከል ከዳር እስከ ዳር ይለፍ።
29 ፤ ሳንቆቹንም በወርቅ ለብጣቸው፤ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ ሥራቸው፤ መወርወሪያዎችንም በወርቅ ለብጣቸው።
30 ፤ ማደሪያውንም በተራራ እንዳሳየሁህ ምሳሌ አቁም።
31 ፤ መጋረጃውንም ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም አድርግ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእርሱ ላይ ይሁኑ።
32 ፤ በወርቅ በተለበጡት ከግራር እንጨትም በተሠሩት በአራቱ ምሰሶች ላይ ስቀለው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ፥ አራቱም እግሮቻቸው ከብር የተሠሩ ይሁኑ።
33 ፤ መጋረጃውንም ከመያዣዎቹ በታች ታንጠለጥለዋለህ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የምስክርን ታቦት አግባው፤ መጋረጃውም በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል መለያ ይሁናችሁ።
34 ፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ የስርየት መክደኛውን በምስክሩ ታቦት ላይ አድርግ።
35 ፤ ገበታውንም በመጋረጃው ውጭ፥ መቅረዙንም በገበታው ፊት ለፊት በማደሪያው በደቡብ ወገን አድርግ፤ ገበታውንም በሰሜን ወገን አድርገው።
36 ፤ ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አድርግለት።
37 ፤ ለመጋረጃውም አምስት ምሰሶች ከግራር እንጨት አድርግ፥ በወርቅም ለብጣቸው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ፤ አምስትም እግሮች አድርግላቸው።