ምዕራፍ 25

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።
2 ፤ ስጦታ ያመጡልኝ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ በገዛ እጁ ሊሰጠኝ በልቡ ከሚያምረው ሰው ሁሉ መባ ተቀበሉ።
3 ፤ ከእነርሱም የምትቀበሉት መባ ይህ ነው፤
4 ፤ ወርቅ፥ ብር፥ ናስም፥ ሰማያዊና ሐምራዊ ቀይም ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም፥
5 ፤ የፍየልም ጠጕር፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበት፥ የአቆስጣ ቁርበት፥ የግራርም እንጨት፥
6 ፤ የመብራትም ዘይት፥ ለቅብዓት ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን ቅመም፥
7 ፤ መረግድም፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ።
8 ፤ በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ።
9 ፤ እኔ እንደማሳይህ ሁሉ፥ እንደ ማደሪያው ምሳሌ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ፥ እንዲሁ ሥሩት።
10 ፤ ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን።
11 ፤ በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት።
12 ፤ አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር፤ በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ።
13 ፤ መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው።
14 ፤ ለታቦቱ መሸከሚያ በታቦቱ ጐን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አግባ።
15 ፤ መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከቶም አይውጡ።
16 ፤ በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ።
17 ፤ ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ።
18 ፤ ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ።
19 ፤ ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ።
20 ፤ ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ።
21 ፤ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ።
22 ፤ በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ።
23 ፤ ርዝመቱም ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ገበታ ከግራር እንጨት ሥራ።
24 ፤ በጥሩም ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አድርግለት፤
25 ፤ በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አድርግለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አድርግለት።
26 ፤ አራትም የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አድርግ።
27 ፤ ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶቹ በክፈፉ አቅራቢያ ይሁኑ።
28 ፤ ገበታውን ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው።
29 ፤ ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ ወጭቶችዋን ጭልፋዎችዋንም መቅጃዎችዋንም ጽዋዎችዋንም አድርግ፤ እነርሱንም ከጥሩ ወርቅ አድርጋቸው።
30 ፤ በገበታም ላይ የገጽ ኅብስት ሁልጊዜ በፊቴ ታደርጋለህ።
31 ፤ መቅረዝንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ፤ መቅረዙ ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀጠቀጠ ሥራ ይደረግ፤ ጽዋዎቹም ጕብጕቦቹም አበቦቹም አንድነት በእርሱ ይደረጉበት።
32 ፤ በስተጎኑ ስድስት ቅርንጫፎች ይውጡለት፤ ሦስት የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስትም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ይውጡ።
33 ፤ በአንደኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፤ እንዲሁም ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አድርግ።
34 ፤ በመቅረዙም ጕብጕቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አድርግ።
35 ፤ ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ይሁን።
36 ፤ ጕብጕቦቹና ቅርንጫፎቹ ሁሉ ከእርሱ ጋር አንድ ይሁኑ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ይደረግ።
37 ፤ ሰባቱንም መብራቶች ሥራ፤ በፊቱ ያበሩ ዘንድ መብራቶቹን ያቀጣጥሉአቸዋል።
38 ፤ መኰስተሪያዎችዋን የኵስታሪ ማድረጊያዎችዋንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ።
39 ፤ መቅረዙም ዕቃውም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ ይሠሩ።
40 ፤ በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ።