ምዕራፍ 24

ሙሴንም። አንተ አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር ውጡ፥ በሩቁም ስገዱ፤
2 ፤ ሙሴም ብቻውን ወደ እግዚአብሔር ይቅረብ፥ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከእርሱ ጋር አይውጡ አለው።
3 ፤ ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ። እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ።
4 ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ፤ ማለዳም ተነሣ፥ ከተራራውም በታች መሠዊያን፥ አሥራ ሁለትም ሐውልቶች ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ሠራ።
5 ፤ የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ለእግዚአብሔርም ስለ ደኅንነት መሥዋዕት በሬዎችን እንዲሠዉ የእስራኤልን ልጆች ጐበዛዝት ሰደደ።
6 ፤ ሙሴም የደሙን እኵሌታ ወስዶ በቆሬ ውስጥ አደረገው፤ የደሙንም እኵሌታ በመሠዊያው ረጨው።
7 ፤ የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም። እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም አሉ።
8 ፤ ሙሴም ደሙን ውስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው። በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ።
9 ፤ ሙሴም አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤
10 ፤ የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ።
11 ፤ እጁንም በእስራኤል አዛውንቶች ላይ አልዘረጋም፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም።
12 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ በዚያም ሁን፤ እነርሱን ታስተምር ዘንድ እኔ የጻፍሁትን ሕግና ትእዛዝ የድንጋይም ጽላት እሰጥሃለሁ አለው።
13 ፤ ሙሴና ሎሌው ኢያሱ ተነሡ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ።
14 ፤ ሽማግሌዎችንም። ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቆዩን፤ አሮንና ሖርም እነሆ ከእናንተ ጋር ናቸው፥ ነገረተኛም ቢኖር ወደ እነርሱ ይምጣ አላቸው።
15 ፤ ሙሴም ወደ ተራራ ወጣ፥ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው።
16 ፤ የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ተቀመጠ፥ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው።
17 ፤ በተራራው ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ።
18 ፤ ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊትም ቆየ።