ምዕራፍ 8

እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው። ወደ ፈርዖን ግባ እንዲህም በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ያገለግለኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
2 ፤ ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ እኔ አገርህን ሁሉ በጓጕንቸሮች እመታለሁ፤
3 ፤ ወንዙም ጓጕንቸሮችን ያፈላል፥ ወጥተውም ወደ ቤትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህም፥ ወደ ባሪያዎችህም ቤት፥ በሕዝብህም ላይ፥ ወደ ምድጆችህም፥ ወደ ቡሃቃዎችህም ይገባሉ፤
4 ፤ ጓጕንቸሮችም በአንተ በሕዝብህም በባሪያዎችም ሁሉ ላይ ይወጣሉ።
5 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ይዘህ በወንዞቹና በመስኖቹ በውኃ ማከማቻዎቹም ላይ እጅህን ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አውጣ በለው።
6 ፤ አሮንም በግብፅ ውኆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮቹም ወጡ፥ የግብፅንም አገር ሸፈኑ።
7 ፤ ጠንቋዮችም በአስማታቸው እንዲህ አደረጉ፥ በግብፅም አገር ላይ ጓጕንቸሮችን አወጡ።
8 ፤ ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ። ጓጕንቸሮቹን ከእኔ ከሕዝቤም እንዲያርቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ለእግዚአብሔርም ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እለቅቃለሁ አላቸው።
9 ፤ ሙሴም ፈርዖንን። ጓጕንቸሮቹ ከአንተ ከቤቶችህም እንዲጠፉ፥ በወንዙም ብቻ እንዲቀሩ፥ ለአንተ ለባሪያዎችህም ለሕዝብህም መቼ እንድጸልይ አስታውቀኝ አለው። እርሱም። ነገ አለ።
10 ፤ ሙሴም። አምላካችንን እግዚአብሔርን የሚመስል እንደሌለ ታውቅ ዘንድ እንደ ቃልህ ይሁን።
11 ፤ ጓጕንቸሮቹም ከአንተ ከቤቶችህም ከባርያዎችህም ከሕዝብህም ይሄዳሉ፤ በወንዙም ብቻ ይቀራሉ አለ።
12 ፤ ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ዘንድ ወጡ፤ ሙሴም በፈርዖን ላይ ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
13 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም ከቤት ከወጀድም ከሜዳም ሞቱ።
14 ፤ እንደ ክምርም አድርገው ሰበሰቡአቸው፤ ምድርም ገማች።
15 ፤ ፈርዖንም ጸጥታ እንደሆነ ባየ ጊዜ ልቡን አደነደነ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ አልሰማቸውም።
16 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። አሮንን። በትርህን ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ሁሉ ቅማል እንዲሆን የምድሩን ትቢያ ምታ በለው።
17 ፤ እንዲሁም አደረጉ፤ አሮንም እጁን ዘረጋ፥ በበትሩም የምድሩን ትቢያ መታው፥ በሰውና በእንስሳም ላይ ቅማል ሆነ፤ በግብፅ አገር ሁሉ የምድር ትቢያ ሁሉ ቅማል ሆነ።
18 ፤ ጠንቋዮችም በአስማታቸው ያወጡ ዘንድ እንዲሁ አደረጉ፥ ነገር ግን አልቻሉም፤ ቅማሉም በሰውና በእንስሳ ላይ ነበረ።
19 ፤ ጠንቋዮችም ፈርዖንን። ይህስ የእግዚአብሔር ጣት ነው አሉት፤ የፈርዖን ልብ ግን ጸና፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም።
20 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ማልደህ ተነሣ፥ በፈርዖንም ፊት ቁም፤ እነሆ እርሱ ወደ ውኃ ይወርዳል፤ እንዲህም በለው። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ።
21 ፤ ሕዝቤንም ባትለቅቅ፥ እነሆ በአንተ በባሪያዎችህም በሕዝብህም በቤቶችህም ላይ የዝንብ መንጎች እሰድዳለሁ፤ የግብፃውያን ቤቶች የሚኖሩባትም ምድር ሁሉ በዝንብ መንጎች ይሞላሉ።
22 ፤ በዚያን ቀን በምድር መካከል እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቅ ዘንድ፥ በዚያ የዝንብ መንጋ እንዳይሆን ሕዝቤ የሚቀመጥባትን የጌሤምን ምድር እለያለሁ።
23 ፤ በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል እለያለሁ፤ ይህም ተአምራት ነገ ይሆናል።
24 ፤ እግዚአብሔርም እንዲሁ አደረገ፤ በፈርዖንም ቤት በባሪያዎቹም ቤቶች ውስጥ ብዙ የዝንብ መንጋ መጣ፤ በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ከዝንቡ መንጋ የተነሣ ምድር ጠፋች።
25 ፤ ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ። ሂዱ፥ በአገሩ ውስጥ ለአምላካችሁ ሠዉ አላቸው።
26 ፤ ሙሴም። ለእግዚአብሔር ለአምላካችን የግብፃውያንን ርኵሰት እንሰዋለንና እንዲህ ይደረግ ዘንድ አይገባም፤ እነሆ እኛ የግብፃውያንን ርኵሰት በፊታቸው ብንሠዋ አይወግሩንምን?
27 ፤ እኛስ ለእግዚአብሔር ለአምላካችን እንሠዋ ዘንድ እንደሚያዝዘን የሦስት ቀን መንገድ ወደ ምድረ በዳ እንሄዳለን አለ።
28 ፤ ፈርዖንም። ለእግዚአብሔር ለአምላካችሁ በምድረ በዳ ትሠዉ ዘንድ እለቅቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ አትሂዱ፥ ጸልዩልኝ አለ።
29 ፤ ሙሴም። እነሆ ከአንተ ዘንድ እወጣለሁ፥ የዝንቡም መንጎች ከፈርዖን ከባሪያዎቹም ከሕዝቡም ነገ እንዲሄዱ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እንዳይለቅቅ ፈርዖን እንደገና አያታልለን አለ።
30 ፤ ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ።
31 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ፤ የዝንቡንም መንጎች ከፈርዖን ከባሪያዎቹም ከህዝቡም አስነሣ፤ አንድ ስንኳ አልቀረም።
32 ፤ ፈርዖንም በዚህ ጊዜ ደግሞ ልቡን አደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።