ምዕራፍ 23

ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል፤ ሐሰተኛ ምስክርም ትሆን ዘንድ ከኃጢአተኛ ጋር እጅህን አታንሣ።
2 ፤ ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጥመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር።
3 ፤ በፍርድ ነገርም ለድሀው አታድላ።
4 ፤ የጠላትህን በሬ ወይም አህያውን ጠፍቶ ብታገኘው በፍጹም መልስለት።
5 ፤ የሚጠላህን ሰው አህያ ከሸክሙ በታች ወድቆ ብታየው አትተወው፥ ነገር ግን ከእርሱ ጋር አንሣው።
6 ፤ በሚምዋገትበት ጊዜ የድሀህን ፍርድ አታጥምም።
7 ፤ ከሐሰት ነገር ራቅ፤ እኔ ኃጢአተኛውን አላጸድቅምና ንጹሕንና ጻድቅን አትግደል።
8 ፤ ማማለጃን አትቀበል፤ ማማለጃ የዓይናማዎችን ሰዎች ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና።
9 ፤ በስደተኛው ግፍ አታድርጉ፤ እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ስለ ነበራችሁ የስደተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች አውቃችኋልና።
10 ፤ ስድስት ዓመት ምድርህን ዝራ፥ ፍሬዋንም አግባ፤
11 ፤ በሰባተኛው ዓመት ግን ተዋት አሳርፋትም፤ የሕዝብህም ድሆች ይበሉታል፤ ያስቀሩትንም የሜዳ እንስሳ ይብላው። እንዲሁም በወይንህና በወይራህ አድርግ።
12 ፤ ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ ያርፉ ዘንድ ለባሪያህም ልጅ ለመጻተኛውም ዕረፍት ይሆን ዘንድ በሰባተኛው ቀን ዕረፍ።
13 ፤ ያልኋችሁንም ነገር ሁሉ ጠብቁ፤ የሌሎችንም አማልክት ስም አትጥሩ፥ ከአፋችሁም አይሰማ።
14 ፤ በዓመት ሦስት ጊዜ በዓል ታደርግልኛለህ።
15 ፤ የቂጣውን በዓል ጠብቅ፤ በአቢብ ወር ከግብፅ ምድር ወጥታችኋልና በዚህ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፤ በፊቴም ባዶ እጃችሁን አትታዩ።
16 ፤ በእርሻም የምትዘራትን የፍሬህን በኵራት የመከር በዓል፥ ዓመቱም ሳያልቅ ፍሬህን ከእርሻ ባከማቸህ ጊዜ የመክተቻውን በዓል ጠብቅ።
17 ፤ በዓመት ሦስት ጊዜ በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ።
18 ፤ የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የበዓሌም ስብ እስኪነጋ አይደር።
19 ፤ የተመረጠውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጣ። ጠቦትን በእናቱ ወተት አትቀቅል።
20 ፤ በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ።
21 ፤ በፊቱ ተጠንቀቁ፥ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት።
22 ፤ አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፥ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ፥ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ።
23 ፤ መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና፥ ወደ አሞራውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ያገባሃል፤ እኔም አጠፋቸዋለሁ።
24 ፤ ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፥ አታምልካቸውም፤ እንደ ሥራቸውም አትሥራ፤ ነገር ግን ፈጽመህ አፍርሳቸው፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብራቸው።
25 ፤ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ታመልኩታላችሁ፥ እርሱም እህልህንና ውኃህን ይባርካል፤ በሽታንም ከመካከልህ አርቃለሁ።
26 ፤ በምድርህም መካን ወይም የምትጨነግፍ አትሆንም፤ የዘመንህን ቍጥር እሞላለሁ።
27 ፤ መፈራቴንም በፊትህ እሰድዳለሁ፥ የምትሄድበትንም ሕዝብ ሁሉ አስደነግጣቸዋለሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ በፊትህ ጀርባቸውን እንዲያዞሩ አደርጋለሁ።
28 ፤ በፊትህም ተርብ እሰድዳለሁ፥ ኤዊያዊውንም ከነዓናዊውንም ኬጢያዊውንም ከፊትህ አባርራለሁ።
29 ፤ ምድር ባድማ እንዳትሆን፥ የምድር አራዊትም እንዳይበዙብህ፥ በአንድ ዓመት ከፊታችሁ አላባርራቸውም።
30 ፤ ነገር ግን እስክትበዛ ምድርንም እስክትወርስ ድረስ በጥቂት በጥቂት አባርራቸዋለሁ።
31 ፤ ድንበርህንም ከኤርትራ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፥ ከምድረ በዳም እስከ ወንዙ ድረስ አደርጋለሁ፤ በምድር የሚኖሩትን በእጅህ እጥላለሁና፤ ከፊትህም ታባርራቸዋለሁ።
32 ፤ ከእነርሱና ከአማልክቶቻቸው ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ።
33 ፤ አማልክቶቻቸውንም ብታመልክ ወጥመድ ይሆኑብሃልና እኔን እንድትበድል እንዳያደርጉህ በአገርህ አይቀመጡ።