ምዕራፍ 36

ለመቅደስም ማገልገያ ሥራ ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እንዲያውቁ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው ባስልኤልና ኤልያብ በልባቸው ጥበበኞችም ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ነገር ሁሉ አደረጉ።
2 ፤ ሙሴም ባስልኤልንና ኤልያብን፥ እግዚአብሔርም በልቡ ጥበብን ያደረገለትን በልብ ጥበበኛ ሰው ሁሉ፥ ሥራውንም ለመሥራት ይቀርብ ዘንድ ልቡ ያስነሣውን ሁሉ ጠራቸው።
3 ፤ እነርሱም የእስራኤል ልጆች ለመቅደስ ማገልገያ ሥራ ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ይሠሩ ዘንድ ከሙሴ ተቀበሉ። እነዚያም እንደ ፈቃዳቸው ማለዳ ማለዳ ስጦታውን ገና ወደ እርሱ ያመጡ ነበር።
4 ፤ የመቅደሱንም ሥራ የሚሠሩ ጠቢባን ሁሉ የሚያደርጉትን ሥራ ትተው መጡ፥
5 ፤ እነርሱም ሙሴን። እግዚአብሔር ለማገልገያ ሥራ ይደረግ ዘንድ ላዘዘው ከሚበቃ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ሕዝቡ አመጡ ብለው ተናገሩት።
6
7 ፤ ያመጡትም ነገር ሥራን ሁሉ ለመፈጸም በቅቶ ገና ይተርፍ ስለ ነበረ ሙሴ አዘዘና። ወንድ ወይም ሴት ለመቅደስ ስጦታ ከዚህ የበለጠ የሚያመጣ አይኑር ብሎ በሰፈሩ ውስጥ አሳወጀ። ሕዝቡም እንዳያመጡ ተከለከሉ። ፕ
8 ፤ በእነርሱም ዘንድ ያሉት ሥራ ሲሠሩ የነበሩት በልባቸው ጥበበኞች ሁሉ ማደሪያውን ከአሥር መጋረጆች ሠሩ፤ እነርሱንም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ሠሩ፤ በእነርሱም ላይ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤልን አደረጉባቸው።
9 ፤ የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ነበረ፤ የመጋረጆቹ ሁሉ ልክ ትክክል ነበረ።
10 ፤ አምስቱንም መጋረጆች እርስ በርሳቸው አጋጠሙ፤ አምስቱንም መጋረጆች እንዲሁ እርስ በርሳቸው አጋጠሙ።
11 ፤ ከሚጋጠሙትም መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አደረጉ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አደረጉ።
12 ፤ አምሳ ቀለበቶችንችን በአንድ መጋረጃ አደረጉ፤ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አደረጉ፤ ቀለበቶቹ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት የሚተያዩ ነበሩ።
13 ፤ አምሳም የወርቅ መያዣዎች ሠሩ፤ መጋረጆችንም እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጠሙአቸው፤ አንድ ማደሪያም ሆነ።
14 ፤ ከማደሪያውም በላይ ለድንኳን የሚሆኑ መጋረጆችን ከፍየል ጠጕር አደረጉ፤ አሥራ አንድ መጋረጆች አደረጉ።
15 ፤ እያንዳንዱም መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ እያንዳንዱም መጋረጃ ወርዱ አራት ክንድ ነበረ፤ የአሥራ አንዱም መጋረጆች መጠናቸው ትክክል ነበረ።
16 ፤ አምስቱንም መጋረጆች እርስ በርሳቸው አንድ አድርገው፥ ስድስቱንም መጋረጆች አንድ አድርገው አጋጠሙአቸው።
17 ፤ ከተጋጠሙትም መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አደረጉ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አደረጉ።
18 ፤ ድንኳኑም አንድ እንዲሆን ያጋጥሙት ዘንድ አምሳ የናስ መያዣዎችን ሠሩ።
19 ፤ ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ ከአውራ በግ ቁርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአቆስጣ ቁርበት አደረጉ።
20 ፤ ለማደሪያውም ከግራር እንጨት የሚቆሙትን ሳንቆች አደረጉ።
21 ፤ የሳንቃው ሁሉ ርዝመቱ አሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ነበረ።
22 ፤ ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ነበሩ፤ ለማደሪያው ሳንቆች ሁሉ እንዲሁ አደረጉ።
23 ፤ ለማደሪያውም በደቡብ ወገን ሀያ ሳንቆችን አደረጉ፤
24 ፤ ከሀያውም ሳንቆች በታች አርባ የብር እግሮች አደረጉ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ለሁለቱ ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ነበሩ።
25 ፤ ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሀያ ሳንቆች አደረጉ፤
26 ፤ ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች፥ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች አደረጉ።
27 ፤ ለማደሪያውም በምዕራቡ ወገበስተ ኋላ ስድስት ሳንቆች አደረጉ።
28 ፤ ለማደሪያውም ለሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቆች አደረጉ።
29 ፤ ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንድ ሳንቃ ድርብ ነበረ፤ ለሁለቱም ማዕዘን እንዲሁ ሁለት ነበሩ።
30 ፤ ስምንት ሳንቆችና አሥራ ስድስቱ የብር እግሮቻቸው፥ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት ሁለት እግሮች ነበሩ።
31 ፤ ከግራርም እንጨት በማደሪያው በአንደኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥
32 ፤ በማደሪያውም በሁለተኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ ከማደሪያውም በስተ ኋላ በምዕራቡ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች አደረጉ።
33 ፤ መካከለኛውንም መወርወሪያ በሳንቆቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር አሳለፉ።
34 ፤ ሳንቆቹንም በወርቅ ለበጡአቸው፤ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ አደረጉ፤ መወርወሪያዎቹንም በወርቅ ለበጡአቸው።
35 ፤ መጋረጃውንም ከሰማያዊና ከሐምራዊ ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረጉ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤልን በእርሱ ላይ አደረጉ።
36 ፤ ከግራርም እንጨት አራት ምሰሶች አደረጉለት፥ በወርቅም ለበጡአቸው፤ ኩላቦቻቸው የወርቅ ነበሩ፤ ለእነርሱም አራት የብር እግሮች አደረጉ።
37 ፤ ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊና ከሐምራዊ ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አደረጉ፤
38 ፤ አምስቱንም ምሰሶች፥ ኩላቦቻቸውንም አደረጉ፤ ጕልላቶቻቸውንና ዘንጎቻቸውንም በወርቅ ለበጡአቸው፤ አምስቱም እግሮቻቸው የናስ ነበሩ።