ምዕራፍ 10

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ሁለት የብር መለከቶች አጠፍጥፈህ ለአንተ አድርግ፤ ማኅበሩን ለመጥራት ከሰፈራቸውም ለማስጓዝ ይሁኑልህ።
3 ፤ ሁለቱም መለከቶች በተነፉ ጊዜ ማኅበሩ ሁሉ ወደ አንተ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይሰብሰቡ።
4 ፤ አንድ መለከት ሲነፋ ታላላቆቹ የእስራኤል አእላፍ አለቆች ወደ አንተ ይሰብሰቡ።
5 ፤ መለከትንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በምሥራቅ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ።
6 ፤ ሁለተኛውንም ከፍ ባለ ድምፅ ስትነፉ በደቡብ በኩል የሰፈሩት ይጓዙ፤ ለማስጓዝ መለከትን ይነፋሉ።
7 ፤ ጉባኤውም በሚሰበሰብበት ጊዜ ንፉ፥ ነገር ግን ድምፁን ከፍ አታድርጉት።
8 ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ መለከቶቹን ይንፉ፤ እነርሱም ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ይሁኑ።
9 ፤ በሚገፋችሁም ጠላት ላይ በምድራችሁ ወደ ሰልፍ ስትወጡ ከፍ ባለ ድምፅ መለከቶቹን ንፉ፤ በእግዚአብሔርም በአምላካችሁ ፊት ትታሰባላችሁ፥ ከጠላቶቻችሁም ትድናላችሁ።
10 ፤ ደግሞ በደስታችሁ ቀን፥ በበዓላታችሁም ዘመን፥ በወርም መባቻ፥ በሚቃጠል መሥዋዕታችሁና በደኅንነት መሥዋዕታችሁ ላይ መለከቶቹን ንፉ፤ እነርሱም በአምላካችሁ ፊት ለመታሰቢያ ይሆኑላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
11 ፤ በሁለተኛውም ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን እንዲህ ሆነ፤ ደመናው ከምስክሩ ማደሪያ ላይ ተነሣ።
12 ፤ የእስራኤልም ልጆች ከሲና ምድረ በዳ በየጕዞአቸው ተጓዙ፤ ደመናውም በፋራን ምድረ በዳ ቆመ።
13 ፤ በመጀመሪያም እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ ተጓዙ።
14 ፤ በመጀመሪያም የይሁዳ ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን አለቃ ነበረ።
15 ፤ በይሳኮርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሶገር ልጅ ናትናኤል አለቃ ነበረ።
16 ፤ በዛብሎንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኬሎን ልጅ ኤልያብ አለቃ ነበረ።
17 ፤ ማደሪያውም ተነቀለ፤ ማደሪያውንም የተሸከሙ የጌድሶን ልጆችና የሜራሪ ልጆች ተጓዙ።
18 ፤ የሮቤልም ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር አለቃ ነበረ።
19 ፤ በስምዖንም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል አለቃ ነበረ።
20 ፤ በጋድም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ አለቃ ነበረ።
21 ፤ ቀዓታውያንም መቅደሱን ተሸክመው ተጓዙ፤ እነዚህም እስኪመጡ ድረስ እነዚያ ማደሪያውን ተከሉ።
22 ፤ የኤፍሬምም ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ አለቃ ነበረ።
23 ፤ በምናሴም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል አለቃ ነበረ።
24 ፤ በብንያምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን አለቃ ነበረ።
25 ፤ ከሰፈሮቹ ሁሉ በኋላ የሆነ የዳን ልጆች ሰፈር ዓላማ በየሠራዊታቸው ተጓዘ፤ በሠራዊቱም ላይ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር አለቃ ነበረ።
26 ፤ በአሴርም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የኤክራን ልጅ ፋግኤል አለቃ ነበረ።
27 ፤ በንፍታሌምም ልጆች ነገድ ሠራዊት ላይ የዔናን ልጅ አኪሬ አለቃ ነበረ።
28 ፤ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ጕዞ በየሠራዊታቸው ነበረ፤ እነርሱም ተጓዙ።
29 ፤ ሙሴም የሚስቱን አባት የምድያማዊውን የራጉኤልን ልጅ ኦባብን። እግዚአብሔር። ለእናንተ እሰጠዋለሁ ወዳለው ስፍራ እንሄዳለን፤ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል መልካምን ነገር ተናግሮአልና አንተ ከእኛ ጋር ና፥ መልካምን እናደርግልሃለን አለው።
30 ፤ እርሱም። አልሄድም፥ ነገር ግን ወደ አገሬና ወደ ዘመዶቼ እሄዳለሁ አለው።
31 ፤ እርሱም። እባክህ፥ በምድረ በዳ የምንሰፍርበትን አንተ ታውቃለህና፥ እንደ ዓይኖቻችንም ትሆንልናለህና አትተወን፤
32 ፤ ከእኛም ጋር ብትሄድ እግዚአብሔር ከሚያደርግልን መልካም ነገር ሁሉ እኛ ለአንተ እናደርጋለን አለ።
33 ፤ ከእግዚአብሔርም ተራራ የሦስት ቀን መንገድ ያህል ተጓዙ፤ የእግዚአብሔርም የኪዳኑ ታቦት የሚያድርበትን ስፍራ ይፈልግላቸው ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ቀደማቸው።
34 ፤ ከሰፈራቸውም በተጓዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ደመና ቀን ቀን በላያቸው ነበረ።
35 ፤ ሙሴም ታቦቱ በተጓዘ ጊዜ። አቤቱ፥ ተነሣ፥ ጠላቶችህም ይበተኑ፥ የሚጠሉህም ከፊትህ ይሽሹ ይል ነበር።
36 ፤ ባረፈም ጊዜ። አቤቱ፥ ወደ እስራኤል እልፍ አእላፋት ተመለስ ይል ነበር።