ምዕራፍ 29

በሰባተኛውም ወር ከወሩ በመጀመሪያ ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፤ መለከቶች የሚነፉበት ቀን ነው።
2 ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
3 ፤ ለእህል ቍርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥
4 ፤ ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ።
5 ፤ ማስተስረያም የሚሆንላችሁን አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ።
6 ፤ በወሩ መባቻ ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ በዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ፥ እንደ ሕጋቸው ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርቡ ናቸው።
7 ፤ ከዚህም ከሰባተኛው ወር በአሥረኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቁት፤ ከሥራ ሁሉ ምንም አታድርጉ።
8 ፤ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤ ነውር የሌለባቸው ይሁኑ።
9 ፤ ለእህል ቍርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለወይፈኑ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራው በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥
10 ፤ ለሰባቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ፥
11 ፤ ለኃጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል አቅርቡ። ከሚያስተሰርየው ከኃጢአት መሥዋዕት፥ በዘወትርም ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን፥ ከመጠጥ ቍርባናቸውም ሌላ አቅርቡት።
12 ፤ ከሰባተኛውም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት፥ ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር በዓል አድርጉ።
13 ፤ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አሥራ ሦስት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ ነውር የሌለባቸውም ይሁኑ።
14 ፤ ለእህል ቍርባናቸውም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለአሥራ ሦስት ወይፈኖች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለሁለቱ አውራ በጎች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥
15 ፤ ለአሥራ አራቱ ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ፥
16 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ የሚቀርቡ ናቸው።
17 ፤ በሁለተኛውም ቀን አሥራ ሁለት ወይፈኖችን፥ ሁለት አውራ በጎችን፥ ነውር የሌለባቸው አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶችን፥
18 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥
19 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየልን ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባናቸው ሌላ የሚቀርቡ ናቸው።
20 ፤ በሦስተኛውም ቀን አሥራ አንድ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
21 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥
22 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
23 ፤ በአራተኛውም ቀን አሥር ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
24 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸውም መጠን እንደ ሕጉ፥
25 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
26 ፤ በአምስተኛውም ቀን ዘጠኝ ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
27 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥
28 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
29 ፤ በስድስተኛውም ቀን ስምንት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
30 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥
31 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
32 ፤ በሰባተኛውም ቀን ሰባት ወይፈኖች፥ ሁለት አውራ በጎች፥ ነውር የሌለባቸውን አሥራ አራት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
33 ፤ ለወይፈኖቹና ለአውራ በጎቹ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባናቸውንና የመጠጥ ቍርባናቸውን እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ፥
34 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፥ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ ታቀርባላችሁ።
35 ፤ በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
36 ፤ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውር የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ።
37 ፤ የእህል ቍርባናቸውና የመጠጥ ቍርባናቸው ለወይፈኑ ለአውራውም በግ ለጠቦቶቹም እንደ ቍጥራቸው መጠን እንደ ሕጉ ይሆናሉ።
38 ፤ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ከመጠጡም ቍርባን ሌላ የሚቀርቡ ናቸው።
39 ፤ እነዚህንም፥ ከስእለታችሁና በፈቃዳችሁ ከምታመጡት ሌላ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእህልም ለመጠጥም ቍርባን፥ ለደኅንነትም መሥዋዕታችሁ በበዓላችሁ ጊዜ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
40 ፤ ሙሴም ለእስራኤል ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ ነገራቸው።