ምዕራፍ 20

የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በመጀመሪያው ወር ወደ ጺን ምድረ በዳ መጡ፤ ሕዝቡም በቃዴስ ተቀመጡ፤ ማርያምም በዚያ ሞተች፥ በዚያም ተቀበረች።
2 ፤ ለማኅበሩም ውኃ አልነበረም፤ በሙሴና በአሮንም ላይ ተሰበሰቡ።
3 ፤ ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት፥ እንዲህም ብለው ተናገሩት። ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር ፊት በሞቱ ጊዜ እኛም ምነው በሞትን ኖሮ!
4 ፤ እኛ ከብቶቻችንም በዚያ እንሞት ዘንድ የእግዚአብሔርን ጉባኤ ወደዚህ ምድረ በዳ ለምን አመጣችሁ?
5 ፤ ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? ዘርና በለስ ወይንም ሮማንም የሌለበት ስፍራ ነው፤ የሚጠጣም ውኃ የለበትም።
6 ፤ ሙሴና አሮንም ከጉባኤው ፊት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሂደው በግምባራቸው ወደቁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው።
7 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
8 ፤ በትርህን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮን ማኅበሩን ሰብስቡ፥ ድንጋዩም ውኃን እንዲሰጥ እነርሱ ሲያዩ ተናገሩት፤ ከድንጋዩም ውኃ ታወጣላቸዋለህ፤ እንዲሁም ማኅበሩን ከብቶቻቸውንም ታጠጣላቸዋለህ።
9 ፤ ሙሴም እንደ ታዘዘ በትሩን ከእግዚአብሔር ፊት ወሰደ።
10 ፤ ሙሴና አሮንም ጉባኤውን በድንጋዩ ፊት ሰብስበው። እናንተ ዓመፀኞች፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ ከዚህ ድንጋይ ውኃን እናወጣላችኋለን? አላቸው።
11 ፤ ሙሴም እጁን ዘርግቶ ድንጋዩን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው፤ ብዙም ውኃ ወጣ፥ ማኅበሩም ከብቶቻቸውም ጠጡ።
12 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን። በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋቸው ምድር ይህን ጉባኤ ይዛችሁ አትገቡም አላቸው።
13 ፤ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ላይ ጠብ ያደረጉበት፥ እርሱም ቅዱስ መሆኑን የገለጠበት ይህ የመሪባ ውኃ ነው።
14 ፤ ሙሴም ከቃዴስ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ መልእክተኞችን እንዲህ ብሎ ላከ። ወንድምህ እስራኤል እንዲህ ይላል። ያገኘንን መከራ ሁሉ አንተ ታውቃለህ፤
15 ፤ አባቶቻችን ወደ ግብፅ ወረዱ፥ በግብፅም እጅግ ዘመን ተቀመጥን ግብፃውያንም እኛንና አባቶቻችንን በደሉ፤
16 ፤ ወደ እግዚአብሔርም በጮኽን ጊዜ ድምፃችንን ሰማ፥ መልአክንም ሰድዶ ከግብፅ አወጣን፤ እነሆም፥ በምድርህ ዳርቻ ባለችው ከተማ በቃዴስ ተቀምጠናል።
17 ፤ እባክህ፥ በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻም ወደ ወይንም አንገባም፥ ከጕድጓዶችም ውኃን አንጠጣም፤ በንጉሡ ጐዳና እንሄዳለን፥ ዳርቻህንም እስክናልፍ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም።
18 ፤ ኤዶምያስም። በሰይፍ እንዳልገጥምህ በምድሬ ላይ አታልፍም አለው።
19 ፤ የእስራኤልም ልጆች። በጐዳናው እንሄዳለን፥ እኔም ከብቶቼም ከውኃህ ብንጠጣ ዋጋውን እንከፍላለን፥ ሌላም ምንም አናደርግም፤ ብቻ በእግራችን እንለፍ አሉት።
20 ፤ እርሱም። አታልፍም አለ። ኤዶምያስም በብዙ ሕዝብና በጽኑ እጅ ሊገጥመው ወጣ።
21 ፤ ኤዶምያስም እስራኤል በዳርቻው እንዳያልፍ ከለከለ፤ ስለዚህ እስራኤል ከእርሱ ተመለሰ።
22 ፤ ከቃዴስም ተጓዙ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ወደ ሖር ተራራ መጡ።
23 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
24 ፤ አሮን ወደ ወገኑ ይከማች፤ በመሪባ ውኃ ዘንድ በቃሌ ላይ ስለ ዐመፃችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደ ሰጠኋት ምድር አይገባም።
25 ፤ አሮንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ ወደ ሖር ተራራ ላይ አምጣቸው፤
26 ፤ ከአሮንም ልብሱን አውጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም ወደ ወገኑ ይከማች፥ በዚያም ይሙት።
27 ፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘ አደረገ፤ ማኅበሩም ሁሉ እያዩ ወደ ሖር ተራራ ወጡ።
28 ፤ ሙሴም የአሮንን ልብስ አወጣ፥ ልጁንም አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም በዚያ በተራራው ራስ ላይ ሞተ፤ ሙሴና አልዓዛርም ከተራራው ወረዱ።
29 ፤ ማኅበሩም ሁሉ አሮን እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ፥ የእስራኤል ቤት ሁሉ ለአሮን ሠላሳ ቀን አለቀሱ።