ምዕራፍ 12

ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ።
2 ፤ እነርሱም። በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን? አሉ፤ እግዚአብሔርም ሰማ።
3 ፤ ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ።
4 ፤ እግዚአብሔርም ወዲያው ሙሴንና አሮንን ማርያምንም። ሦስታችሁ ወደ መገኛኛው ድንኳን ውጡ ብሎ ተናገረ፤ ሦስቱም ወጡ።
5 ፤ እግዚአብሔርም በደመና ዓምድ ወረደ፥ በድንኳኑም ደጃፍ ቆመ፤ አሮንንና ማርያምን ጠራ፥ ሁለቱም ወጡ።
6 ፤ እርሱም። ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ።
7 ፤ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው።
8 ፤ እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥ በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም? አለ።
9 ፤ እግዚአብሔርም ተቈጥቶባቸው ሄደ።
10 ፤ ደመናውም ከድንኳኑ ተነሣ፤ እነሆም፥ ማርያም ለምጻም ሆነች፥ እንደ አመዳይም ነጭ ሆነች፤ አሮንም ማርያምን ተመለከተ፥ እነሆም፥ ለምጻም ሆና ነበር።
11 ፤ አሮንም ሙሴን። ጌታዬ ሆይ፥ ስንፍና አድርገናልና፥ በድለንማልና እባክህ፥ ኃጢአት አታድርግብን።
12 ፤ ከእናቱ ሆድ በወጣ ጊዜ ግማሽ ሥጋው ተበልቶ እንደ ሞተ እርስዋ አትሁን።
13 ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር እየጮኸ። አቤቱ፥ እባክህ፥ አድናት አለው።
14 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። አባትዋ ምራቁን በፊትዋ ቢተፋባት ስንኳ ሰባት ቀን ታፍር ዘንድ ይገባት ነበር፤ ሰባት ቀን ከሰፈር ውጭ ተዘግታ ትቀመጥ፥ ከዚያም በኋላ ትመለስ አለው።
15 ፤ ማርያምም ከሰፈር ውጭ ሰባት ቀን ተዘግታ ተቀመጠች፤ ማርያምም እስክትመለስ ድረስ ሕዝቡ አልተጓዙም።
16 ፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡ ከሐጼሮት ተጓዙ፥ በፋራንም ምድረ በዳ ሰፈሩ።