ምዕራፍ 34

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ ርስት ትሆናችሁ ዘንድ በዕጣ የምትደርሳችሁ ምድር፥ በዳርቻዋ ያለች የከነዓን ምድር፥
3 ፤ ይህች ናት፤ የደቡቡ ወገን ከጺን ምድረ በዳ በኤዶምያስ በኩል ይሆናል፤ የደቡቡም ዳርቻ ከጨው ባሕር ዳር በምሥራቅ በኩል ይጀምራል፤
4 ፤ ዳርቻችሁም በአቅረቢም ዐቀበት በደቡብ በኩል ይዞራል ወደ ጺንም ያልፋል፤ መውጫውም በቃዴስ በርኔ በደቡብ በኩል ይሆናል፤ ወደ ሐጸርአዳር ይሄዳል ወደ ዓጽሞንም ያልፋል፤
5 ፤ ዳርቻውም ከዓጽሞን ወደ ግብፅ ወንዝ ይዞራል፥ መውጫውም በባሕሩ በኩል ይሆናል።
6 ፤ ለምዕራብም ዳርቻ ታላቁ ባሕር ዳርቻችሁ ይሆናል፤ ይህ የምዕራብ ዳርቻችሁ ይሆናል።
7 ፤ የሰሜንም ዳርቻችሁ ይህ ይሆናል፤ ከታላቁ ባሕር ወደ ሖር ተራራ ምልክት ታመለክታላችሁ፤
8 ፤ ከሖርም ተራራ ወደ ሐማት መግቢያ ምልክት ታመለክታላችሁ የዳርቻውም መውጫ በጽዳድ ይሆናል፤
9 ፤ ዳርቻውም ወደ ዚፍሮን ያልፋል እስከ ሐጸርዔናንም ድረስ ይወጣል፤ ይህ የሰሜን ዳርቻችሁ ይሆናል።
10 ፤ የምሥራቁንም ዳርቻችሁን ከሐጸርዔናን ወደ ሴፋማ ምልክት ታመለክታላችሁ፤
11 ፤ ዳርቻውም ከሴፋማ በዓይን ምሥራቅ ወዳለው ወደ ሪብላ ይወርዳል፤ እስከ ኪኔሬት የባሕር ወሽመጥ በምሥራቅ በኩል ይደርሳል፤
12 ፤ ዳርቻውም ወደ ዮርዳኖስ ይወርዳል፥ መውጫውም በጨው ባሕር ይሆናል። ምድራችሁ እንደ ዳርቻዋ በዙሪያዋ ይህች ናት።
13 ፤ ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። እግዚአብሔር ለዘጠኝ ነገድ ተኩል ይሰጡአቸው ዘንድ ያዘዘ በዕጣ የምትወርሱአት ምድር ይህች ናት፤
14 ፤ የሮቤልም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የጋድም ልጆች ነገድ በየአባቶቻቸው ቤት፥ የምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን ወርሰዋል።
15 ፤ እነዚህ ሁለቱ ነገድና የአንዱ ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን በዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ አንጻር በምሥራቅ በኩል ወረሱ።
16 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
17 ፤ ምድሪቱን ርስት አድርገው የሚከፍሉላችሁ ሰዎች ስማቸው ይህ ነው፤ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ።
18 ፤ ምድሪቱንም ርስት አድርገው ይከፍሉ ዘንድ ከየነገዱ አንድ አንድ አለቃ ትወስዳላችሁ።
19 ፤ የሰዎቹም ስም ይህ ነው፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፥
20 ፤ ከስምዖን ልጆች ነገድ የዓሚሁድ ልጅ ሰላሚኤል፥
21 ፤ ከብንያም ነገድ የኪስሎን ልጅ ኤልዳድ፥
22 ፤ ከዳን ልጆች ንገድ አንድ አለቃ የዮግሊ ልጅ ቡቂ፥
23 ፤ ከዮሴፍም ልጆች ከምናሴ ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሱፊድ ልጅ አኒኤል፥
24 ፤ ከኤፍሬም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሺፍጣን ልጅ ቀሙኤል፥
25 ፤ ከዛብሎን ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የፈርናክ ልጅ ኤሊሳፈን፥
26 ፤ ከይሳኮር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሖዛ ልጅ ፈልጢኤል፥
27 ፤ ከአሴር ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የሴሌሚ ልጅ አሒሁድ፥
28 ፤ ከንፍታሌም ልጆች ነገድ አንድ አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ፈዳሄል።
29 ፤ እግዚአብሔር በከነዓን ምድር ለእስራኤል ልጆች ርስታቸውን ይከፍሉ ዘንድ ያዘዛቸው እነዚህ ናቸው።