ምዕራፍ 3

እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ።
2 ፤ የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው፤ በኵሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር።
3 ፤ የተቀቡ ካህናት በክህነትም ያገለግሉ ዘንድ የቀደሳቸው የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው።
4 ፤ ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በእግዚአብሔር ፊት ልዩ እሳት ባቀረቡ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር በአባታቸው በአሮን ፊት በክህነት ያገለግሉ ነበር።
5 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
6 ፤ የሌዊን ነገድ አቅርበህ ያገለግሉት ዘንድ በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው።
7 ፤ የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ እርሱንና ማኅበሩን ሁሉ ለማገልገል የሚያስፈልገውን ነገር በመገናኛው ድንኳን ፊት ይጠብቁ።
8 ፤ የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ ይጠብቁ፥ የእስራኤልን ልጆች ለማገልገል የሚያስፈልገውንም ነገር ይጠብቁ።
9 ፤ ሌዋውያንንም ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣለህ፤ ከእስራኤል ልጆች ለእርሱ ፈጽመው ተሰጡ።
10 ፤ አሮንንና ልጆቹን አቁማቸው፥ ክህነታቸውንም ይጠብቁ፤ ሌላ ሰውም ቢቀርብ ይገደል።
11 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
12 ፤ እነሆ፥ እኔ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ማኅፀን በሚከፍተው በበኵሩ ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤
13 ፤ በኵር ሁሉ ለእኔ ነውና ሌዋውያን ለእኔ ይሁኑ፤ በግብፅ ምድር በኵርን ሁሉ በመታሁ ቀን፥ ከእስራኤል ዘንድ በኵርን ሁሉ፥ ሰውንና እንስሳን፥ ለእኔ ለይቼአለሁ፤ ለእኔ ይሁኑ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
14 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
15 ፤ የሌዊን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገናቸውም ቍጠር፤ ወንዱን ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ቍጠራቸው።
16 ፤ ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዳዘዘው ቈጠራቸው።
17 ፤ የሌዊ ልጆች በየስማቸው እነዚህ ናቸው፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ።
18 ፤ የጌድሶንም ልጆች ስሞች በየወገናቸው እነዚህ ናቸው፤ ሎቤኒ፥ ሰሜኢ።
19 ፤ የቀዓትም ልጆች በየወገናቸው እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል።
20 ፤ የሜራሪም ልጆች በየወገናቸው፤ ሞሖሊ፥ ሙሲ። የሌዋውያን ወገኖች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ናቸው።
21 ፤ ለጌድሶን የሎቤናውያን ወገን የሰሜአውያንም ወገን ነበሩት፤ የጌድሶናውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው።
22 ፤ ከእነርሱ የተቈጠሩት የወንዶች ሁሉ ቍጥር ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
23 ፤ የጌድሶናውያን ወገኖች ከማደሪያው በኋላ በምዕራብ ብኩል ይሰፍራሉ።
24 ፤ የጌድሶናውያንም አባቶች ቤት አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል።
25 ፤ ጌድሶናውያንም በመገናኛው ድንኳን የሚጠብቁት ማደሪያው፥ ድንኳኑም፥ መደረቢያውም፥ የመገናኛው ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥
26 ፤ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለው የአደባባዩ መጋረጆች፥ የአደባባዩም ደጃፍ መጋረጃ፥ ለማገልገሉም ያሉት ገመዶች ሁሉ ይሆናል።
27 ፤ ከቀዓትም የእንበረማውያን ወገን፥ የይስዓራውያንም ወገን፥ የኬብሮናውያንም ወገን፥ የዑዝኤላውያንም ወገን ነበሩ፤ የቀዓታውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው።
28 ፤ ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ፤ መቅደሱንም ይጠብቁ ነበር።
29 ፤ የቀዓት ልጆች ወገኖች በማደሪያው አጠገብ በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ።
30 ፤ የቀዓታውያንም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊሳፈን ይሆናል።
31 ፤ ታቦቱንም፥ ገበታውንም፥ መቅረዙንም፥ መሠዊያዎቹንም፥ የሚያገለግሉበትንም የመቅደሱን ዕቃ፥ መጋረጃውንም፥ ማገልገያውንም ሁሉ ይጠብቃሉ።
32 ፤ የሌዋውያንም አለቆች አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ይሆናል፤ እርሱም መቅደሱን በሚጠብቁት ላይ ይሆናል።
33 ፤ ከሜራሪ የሞሖላውያን ወገን የሙሳያውያንም ወገን ነበሩ፤ የሜራሪ ወገኖች እነዚህ ናቸው።
34 ፤ ከእነርሱም ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
35 ፤ የሜራሪም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ነበረ፤ በማደሪያው አጠገብ በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ።
36 ፤ የሜራሪም ልጆች የሚጠብቁት የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎችም፥ ተራዳዎችም፥ እግሮቹም፥ ዕቃውም ሁሉ፥
37 ፤ ማገልገያውም ሁሉ፥ በዙሪያውም የሚቆሙ የአደባባይ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም ይሆናሉ።
38 ፤ በማደሪያውም ፊት በምሥራቅ በኩል በመገናኛው ድንኳን ፊት በስተ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት ሙሴና አሮን ልጆቹም ይሆናሉ፥ መቅደሱንም ለእስራኤል ልጆች ይጠብቃሉ፤ ልዩም ሰው ቢቀርብ ይገደል።
39 ፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ ከሌዋውያን ወንዶች ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ በየወገናቸው የተቈጠሩት ሁሉ ሀያ ሁለት ሺህ ነበሩ።
40 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የእስራኤልን ልጆች ወንዱን በኵር ሁሉ ቍጠር፤ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን የስማቸውን ቍጥር ውሰድ፤
41 ፤ ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኵር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ለእግዚአብሔር ውሰድ አለው።
42 ፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኵር ሁሉ ቈጠረ።
43 ፤ ከእነርሱም የተቈጠሩ ወንዶች በኵሮች ሁሉ የበስማቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ።
44 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
45 ፤ ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
46 ፤ በሌዋውያን ላይ ከእስራኤል ልጆች በኵር ስለ ተረፉት ስለ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ቤዛ፥ በየራሱ አምስት ሰቅል ውሰድ፤
47 ፤ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ትወስዳለህ፤ ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ነው።
48 ፤ ስለ ተረፉትም የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።
49 ፤ ሙሴም በሌዋውያን ከተቤዡት በላይ ከተረፉት ዘንድ የመቤዣውን ገንዘብ ወሰደ።
50 ፤ ከእስራኤል ልጆች በኵሮች ገንዘቡን ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ወሰደ።
51 ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል፥ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፥ ሙሴ የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።