ምዕራፍ 13

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች የምሰጣትን የከንዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ሰዎችን ላክ፤ ከአባቶች ነገድ ሁሉ እያንዳንዱ በመካከላቸው አለቃ የሆነ አንድ ሰው ትልካላችሁ።
3 ፤ ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ ላካቸው፤ እነርሱም ሁሉ የእስራኤል ልጆች አለቆች ነበሩ።
4 ፤ ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ከሮቤል ነገድ የዘኩር ልጅ ሰሙኤል፤
5 ፤ ከስምዖን ነገድ የሱሬ ልጅ ሰፈጥ፤
6 ፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤
7 ፤ ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ይግአል፤
8 ፤ ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ አውሴ፤
9
10 ፤ ከብንያም ነገድ የራፉ ልጅ ፈልጢ፤ ከዛብሎን ነገድ የሰዲ ልጅ ጉዲኤል፤
11 ፤ ከዮሴፍ ነገድ እርሱም የምናሴ ነገድ የሱሲ ልጅ ጋዲ፤
12 ፤ ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ ዓሚኤል፤
13 ፤ ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሰቱር፤
14 ፤ ከንፍታሌም ነገድ የያቢ ልጅ ናቢ፤
15 ፤ ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ጉዲኤል።
16 ፤ ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ሙሴ የላካቸው ሰዎች ስም ይህ ነው። ሙሴም የነዌን ልጅ አውሴን ኢያሱ ብሎ ጠራው።
17 ፤ ሙሴም የከነዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ላካቸው፥ አላቸውም። ከዚህ በደቡብ በኩል ውጡ፥ ወደ ተራሮችም ሂዱ፤
18 ፤ ምድሪቱንም እንዴት እንደ ሆነች፥ በእርስዋም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥
19 ፤ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ፥ የሚኖሩባትም ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ሰፈሮች ወይም አምቦች እንደ ሆኑ፥
20 ፤ ምድሪቱም ወፍራም ወይም ስስ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች እዩ፤ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤ አይዞአችሁ። በዚያን ጊዜም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ወራት ነበረ።
21 ፤ ወጡም ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ በሐማት ዳር እስካለችው እስከ ረአብ ድረስ ሰለሉ።
22 ፤ በደቡብም በኩል ውጡ፥ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ልጆች አኪመን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብፅ ካለችው ከጣኔዎስ በፊት ሰባት ዓመት ተሠርታ ነበር።
23 ፤ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጡ፥ ከዚያም ከወይኑ አንድ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፥ ሁለቱም ሰዎች በመሎጊያ ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ።
24 ፤ የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የኤሽኮል ሸለቆ ብለው ጠሩት።
25 ፤ ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ።
26 ፤ በፋራን ምድረ በዳና በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሄደው ደረሱ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው።
27 ፤ እንዲህም ብለው ነገሩት። ወደ ላክኸን ምድር ደረስን፥ እርስዋም ወተትና ማር ታፈስሳለች፥ ፍሬዋም ይህ ነው።
28 ፤ ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው። ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም የጸኑ ናቸው፤ ደግሞም በዚያ የዔናቅን ልጆች አየን።
29 ፤ በደቡብም ምድር አማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮቹም ኬጢያዊና ኢያቡሳዊ አሞራዊም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ አጠገብ ተቀምጦአል።
30 ፤ ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና። ማሸነፍ እንችላለንንና እንውጣ፥ እንውረሰው አለ።
31 ፤ ከእርሱ ጋር የወጡ ሰዎች ግን። በኃይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም አሉ።
32 ፤ ስለ ሰለሉአትም ምድር ክፉ ወሬ ለእስራኤል ልጆች እያወሩ። እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት፤ በእርስዋም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው።
33 ፤ በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም፥ የዔናቅን ልጆች፥ አየን፤ እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን፥ ደግሞም እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን አሉ።