ምዕራፍ 25

እስራኤልም በሰጢም ተቀመጡ፤ ሕዝቡም ከሞዓብ ልጆች ጋር ያመነዝሩ ጀመር።
2 ፤ ሕዝቡንም ወደ አምላኮቻቸው መሥዋዕት ጠሩ፤ ሕዝቡም በሉ፥ ወደ አምላኮቻቸውም ሰገዱ።
3 ፤ እስራኤልም ብዔልፌጎርን ተከተለ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ።
4 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የእግዚአብሔር የቍጣው ጽናት ከእስራኤል እንዲመለስ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ ወስደህ በፀሐዩ ፊት ወደ እግዚአብሔር ስቀላቸው አለው።
5 ፤ ሙሴም የእስራኤልን ዳኞች። እናንተ ሁሉ ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሰዎቻችሁን ግደሉ አላቸው።
6 ፤ እነሆም፥ ከእስራኤል ልጆች አንዱ መጥቶ በሙሴና በእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ፊት ምድያማዊቱን አንዲቱን ሴት ወደ ወንድሞቹ አመጣት፤ እነርሱም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ያለቅሱ ነበር።
7 ፤ የካህኑም የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ ባየው ጊዜ ከማኅበሩ መካከል ተነሥቶ በእጁ ጦር አነሣ፤
8 ፤ ያንንም የእስራኤልን ሰው ተከትሎ ወደ ድንኳኑ ገባ። እስራኤላዊውንም ሰውና ሴቲቱን ሁለቱን ሆዳቸውን ወጋቸው። ከእስራኤልም ልጆች መቅሠፍቱ ተከለከለ።
9 ፤ በመቅሠፍትም የሞተው ሀያ አራት ሺህ ነበረ።
10 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
11 ፤ የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በቅንዓቴ በመካከላቸው ቀንቶአልና ቍጣዬን ከእስራኤል ልጆች መለሰ፤ እኔም የእስራኤልን ልጆች በቅንዓቴ አላጠፋሁም።
12 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ የሰላሜን ቃል ኪዳን እሰጠዋለሁ።
13 ፤ ለአምላኩም ቀንቶአልና፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተስርዮአልና ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘላለም ክህነት ቃል ኪዳን ይሆንለታል።
14 ፤ ከምድያማዊቱም ጋር የተገደለው የእስራኤላዊው ሰው ስም ዘንበሪ ነበረ፤ የአባቱ ቤት አለቃ የስምዖናውያን የሆነ የሰሉ ልጅ ነበረ።
15 ፤ የተገደለችውም ምድያማዊት ስምዋ ከስቢ ነበረ፤ እርስዋም የሱር ልጅ ነበረች፤ እርሱም በምድያም ዘንድ የአባቱ ቤት ወገን አለቃ ነበረ።
16 ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
17
18 ፤ በፌጎር በመቅሠፍቱ ቀን ስለተገደለችው ስለ ምድያም አለቃ ልጅ ስለ እኅታቸው ስለ ከስቢ በፌጎር ምክንያት በሸነገሉአችሁ ሽንገላ አስጨንቀዋችኋልና ምድያማውያንን አስጨንቁአቸው ግደሉአቸውም።