ምዕራፍ 28

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። መብሌን፥ ለእኔ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የተደረገውን ቍርባኔን፥ መባዬን በየጊዜው ታቀርቡልኝ ዘንድ ጠብቁ።
3 ፤ እንዲህም በላቸው። በእሳት ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት ቍርባን ይህ ነው፤ ለዘወትር ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ዕለት ዕለት ታቀርባላችሁ።
4 ፤ አንዱን ጠቦት በማለዳ፥ ሌላውንም ጠቦት በማታ አቅርብ፤
5 ፤ ለእህልም ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት ታቀርባለህ።
6 ፤ በእሳት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የቀረበ በሲና ተራራ የተሠራ ለዘወትር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።
7 ፤ የመጠጡ ቍርባን ለአንድ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛው እጅ ነው፤ በመቅደሱ ውስጥ ለእግዚአብሔር ለመጠጥ ቍርባን መጠጥ ታፈስሳለህ።
8 ፤ ሌላውንም ጠቦት በማታ ጊዜ ታቀርባለህ፤ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን በማለዳ እንዳቀረብህ በእሳት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ታቀርበዋለህ።
9 ፤ በሰንበትም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለእህልም ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥ የመጠጡንም ቍርባን ታቀርባላችሁ።
10 ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ፥ በየሰንበቱ ሁሉ የምታቀርቡት የሚቃጠለው መሥዋዕት ይህ ነው።
11 ፤ በወሩም መባቻ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውርም የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
12 ፤ ለእያንዳንዱም ወይፈን ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ መልካም ዱቄት፥ ለአውራው በግም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥
13 ፤ ለእያንዳንዱም ጠቦት ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት ታቀርባላችሁ።
14 ፤ የመጠጥ ቍርባናቸውም ለአንድ ወይፈን የኢን ግማሽ፥ ለአውራው በግም የኢን ሢሶ፥ ለአንዱም ጠቦት የኢን አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ይሆናል፤ ይህ ለዓመቱ የወር መባቻ ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።
15 ፤ ለእግዚአብሔርም ለኃጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከመጠጡ ቍርባን ሌላ ይቀርባል።
16 ፤ በመጀመሪያው ወር ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው።
17 ፤ ከዚህም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ።
18 ፤ በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆናል፤ በእርሱም የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
19 ፤ በእሳትም የተደረገውን ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፤ ነውር የሌለባቸው ይሁኑላችሁ።
20 ፤ የእህል ቍርባናቸውንም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለአንድ ወይፈን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራውም በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥
21 ፤ ለሰባቱም ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ጠቦት ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ።
22 ፤ ማስተስረያ የሚሆንላችሁን አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ።
23 ፤ ማልዶ ከሚቀርበው በዘወትር ከሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ እነዚህን ታቀርባላችሁ።
24 ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚደረገውን የቍርባኑን መብል ሰባት ቀን በየዕለቱ እንዲሁ ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከመጠጡ ቍርባን ሌላ ይቀርባል።
25 ፤ በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
26 ፤ ደግሞ በበኵራት ቀን ከሰባቱ ሱባዔ በዓላችሁ አዲሱን የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ባቀረባችሁ ጊዜ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
27 ፤ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥
28 ፤ ለእህል ቍርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለእያንዳንዱ ወይፈን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአንዱም አውራ በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥
29 ፤ ለሰባቱም ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ጠቦት ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ።
30 ፤ ማስተስረያ የሚሆንላችሁን አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ።
31 ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ሌላ እነርሱንና የመጠጥ ቍርባናቸውን ታቀርባላችሁ፤ ነውርም የሌለባቸው ይሁኑ።