ምዕራፍ 2

እግዚአብሔርም ለሙሴና ለአሮን እንዲህ ብሎ ተናገረ።
2 ፤ የእስራኤል ልጆች እያንዳንዱ በየዓላማው በየአባቶቻቸው ቤቶች ምልክት ይስፈሩ፤ በመገናኛው ድንኳን አፋዛዥ ዙሪያ ይስፈሩ።
3 ፤ በምሥራቅ በኩል ወደ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት እንደ ሠራዊቶቻቸው የይሁዳ ሰፈር ዓላማ ሰዎች ይሆናሉ፤ የይሁዳ ልጆችም አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ።
4 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
5 ፤ በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የይሳኮር ነገድ ይሆናሉ፤ የይሳኮርም ልጆች አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል ነበረ።
6 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
7 ፤ በእነርሱም አጠገብ የዛብሎን ነገድ ነበረ፤ የዛብሎንም ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ነበረ።
8 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
9 ፤ ከይሁዳ ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ሰማንያ ስድስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። እነዚህም አስቀድመው ይጓዛሉ።
10 ፤ በደቡብ በኩል በየሠራዊቶቻቸው የሮቤል ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የሮቤልም ልጆች አለቃ የሰዲዮር ልጅ ኤሊሱር ነበረ።
11 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
12 ፤ በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የስምዖን ነገድ ናቸው፤ የስምዖንም ልጆች አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ነበረ።
13 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ።
14 ፤ በእነርሱም አጠገብ የጋድ ነገድ ነበረ፤ የጋድም ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ነበረ።
15 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ አምሳ ነበሩ።
16 ፤ ከሮቤል ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ አምሳ አንድ ሺህ አራት መቶ አምሳ ነበሩ። እነርሱም ቀጥለው ይጓዛሉ።
17 ፤ ከዚያም በኋላ የመገናኛው ድንኳን በሰፈሮቹም መካከል የሌዋውያን ሰፈር ይጓዛል፤ እንደ ሰፈራቸው ሰው ሁሉ በየስፍራው በየዓላማውም ይጓዛሉ።
18 ፤ በምዕራብ በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የኤፍሬም ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የኤፍሬም ልጆች አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ነበረ።
19 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
20 ፤ በእነርሱም አጠገብ የምናሴ ነገድ ይሆናል፤ የምናሴም ልጆች አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ነበረ።
21 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።
22 ፤ በእነርሱም አጠገብ የብንያም ነገድ ይሆናል፤ ይብንያምም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ነበረ።
23 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
24 ፤ ከኤፍሬም ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ በየሠራዊቶቻቸው መቶ ስምንት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። እነርሱም ሦስተኛ ሆነው ይጓዛሉ።
25 ፤ በሰሜን በኩል እንደ ሠራዊቶቻቸው የዳን ሰፈር ዓላማ ይሆናል፤ የዳንም ልጆች አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ነበረ።
26 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ ስድሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ።
27 ፤ በእነርሱም አጠገብ የሚሰፍሩ የአሴር ነገድ ይሆናሉ፤ የአሴርም ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ነበረ።
28 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።
29 ፤ በእነርሱም አጠገብ የንፍታሌም ነገድ ይሆናል፤ የንፍታሌምም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ነበረ።
30 ፤ ሠራዊቱም፥ ከእነርሱም የተቈጠሩ አምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ።
31 ፤ ከዳን ሰፈር የተቈጠሩ ሁሉ መቶ አምሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። እነርሱም በየዓላሞቻቸው በመጨረሻ ይጓዛሉ።
32 ፤ ከእስራኤል ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች የተቈጠሩ እነዚህ ናቸው፤ ከየሰፈሩ በየሠራዊቶቻቸው የተቈጠሩ ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ነበሩ።
33 ፤ ሌዋውያን ግን እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ከእስራኤል ልጆች ጋር አልተቈጠሩም።
34 ፤ የእስራኤል ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ በዓላሞቻቸው አጠገብ ሰፈሩ፥ እንዲሁም በየወገኖቻቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች ተጓዙ።