ምዕራፍ 6

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው። ሰው ወይም ሴት ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ያደርግ ዘንድ የናዝራዊነት ስእለት ቢሳል፥
3 ፤ ከወይን ጠጅና ከሚያሰክር መጠጥ ራሱን የተለየ ያድርግ፤ ከወይን ወይም ከሌላ ነገር የሚገኘውን ሆምጣጤ አይጠጣ፥ የወይንም ጭማቂ አይጠጣ፤ የወይን እሸት ወይም ዘቢብ አይብላ።
4 ፤ ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ከወይን የሆነውን ነገር ሁሉ ከውስጡ ፍሬ ጀምሮ እስከ ገፈፎው ድረስ አይብላ።
5 ፤ ራሱን ለመለየት ስእለት ባደረገበት ወራት ሁሉ በራሱ ላይ ምላጭ አይደርስም፤ ለእግዚአብሔር የተለየበት ወራት እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰ ይሆናል፥ የራሱንም ጠጕር ያሳድጋል።
6 ፤ ለእግዚአብሔር ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ወደ ሬሳ አይቅረብ።
7 ፤ ለአምላኩ ያደረገው እስለት በራሱ ላይ ነውና አባቱ ወይም እናቱ ወይም ወንድሙ ወይም እኅቱ ሲሞቱ ሰውነቱን አያርክስባቸው።
8 ፤ ራሱን የተለየ ባደረገበት ወራት ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነው።
9 ፤ ሰውም በአጠገቡ ድንገት ቢሞት የተለየውንም ራሱን ቢያረክስ፥ እርሱ በሚነጻበት ቀን ራሱን ይላጭ፤ በሰባተኛው ቀን ይላጨው።
10 ፤ በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ያምጣ፤
11 ፤ ካህኑም አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርበዋል፤ በሬሳም የተነሣ ኃጢአት ሠርቶአልና ያስተሰርይለታል፥ በዚያም ቀን ራሱን ይቀድሰዋል።
12 ፤ ራሱን የተለየ ያደረገበትን ወራትም ለእግዚአብሔር ይቀድሳል፥ የአንድ ዓመትም ተባት ጠቦት ለበደል መሥዋዕት ያምጣ፤ ናዝራዊነቱ ግን ረክሶአልና ያለፈው ወራት ሁሉ ከንቱ ይሆናል።
13 ፤ የመለየቱ ወራት በተፈጸመ ጊዜ የናዝራዊው ሕግ ይህ ነው፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይቅረብ፤
14 ፤ ቍርባኑንም ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለባትን የአንድ ዓመት እንስት ጠቦት ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ነውርም የሌለበትን አውራ በግ ለደኅንነት መሥዋዕት፥
15 ፤ አንድ ሌማትም ቂጣ እንጀራ፥ በዘይት የተለወሰ ከመልካም ዱቄትም የተሠሩ እንጐቻዎች፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ የእህሉንም ቍርባን፥ የመጠጡንም ቍርባን ያቅርብ።
16 ፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባቸዋል፥ የኃጢአቱንም መሥዋዕት የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ያሳርግለታል።
17 ፤ አውራውንም በግ ለደኅንነት መሥዋዕት ከሌማቱ ቂጣ እንጀራ ጋር ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል፤ ካህኑም ደግሞ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን ያቀርባል።
18 ፤ ናዝራዊውም የተለየውን የራሱን ጠጕር በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ይላጫል፥ የመለየቱንም ራስ ጠጕር ወስዶ ከደኅንነት መሥዋዕት በታች ወዳለው እሳት ይጥለዋል።
19 ፤ ካህኑም የተቀቀለውን የአውራውን በግ ወርች፥ ከሌማቱም አንድ ቂጣ እንጐቻ አንድም ስስ ቂጣ ይወስዳል፥ የተለየውንም የራስ ጠጕር ከተላጨ በኋላ በናዝራዊው እጆች ላይ ያኖራቸዋል፤
20 ፤ ካህኑም እነዚህን ለመወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ ይህም ከሚወዘወዘው ፍርምባና ከሚነሣው ወርች ጋር ለካህኑ የተቀደሰ ነው። ከዚያም በኋላ ናዝራዊው ወይን ይጠጣ ዘንድ ይችላል።
21 ፤ ስእለቱን የተሳለው የናዝራዊ፥ እጁም ከሚያገኘው ሌላ ስለ ናዝራዊነቱ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የቍርባኑ ሕግ ይህ ነው፤ ስእለቱን እንደ ተሳለ እንደ ናዝራዊነቱ ሕግ እንዲሁ ያደርጋል።
22 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
23 ፤ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው። የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩአቸው እንዲህ በሉአቸው።
24 ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም፤
25 ፤ እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም፤
26 ፤ እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ ሰላምንም ይስጥህ።
27 ፤ እንዲሁ ስሜን በእስራኤል ልጆች ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እባርካቸዋለሁ።