ምዕራፍ 36

ከዮሴፍ ልጆች ወገኖች የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጆች ወገን አለቆች ቀረቡ፥ በሙሴና በእስራኤልም ልጆች አባቶች አለቆች ፊት ተናገሩ፤
2 ፤ አሉም። ምድሪቱን ለእስራኤል ልጆች ርስት አድርገህ በዕጣ ከፍለህ ትሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር አንተን ጌታችንን አዘዘህ፤ እግዚአብሔርም የወንድማችንን የሰለጰዓድን ርስት ለሴቶች ልጆቹ ትሰጥ ዘንድ አንተን ጌታችንን አዘዘ።
3 ፤ ከሌላም ከእስራኤል ልጆች ነገድ ባል ቢያገቡ፥ ርስታቸው ከአባቶቻችን ርስት ይነቀላል፥ እነርሱም ለሚሆኑበት ለሌላው ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም የርስታችን ዕጣ ይጐድላል።
4 ፤ ለእስራኤልም ልጆች ኢዮቤልዩ በመጣ ጊዜ ርስታቸው ለሚሆኑበት ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም ርስታቸው ከአባቶቻችን ነገድ ርስት ይጐድላል።
5 ፤ ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። የዮሴፍ ልጆች ነገድ በእውነት ተናገሩ።
6 ፤ እግዚአብሔር ስለ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ የወደዱትን ያግቡ፤ ነገር ግን ከአባታቸው ነገድ ብቻ ያግቡ።
7 ፤ እንደዚህም የእስራኤል ልጆች ርስት ከነገድ ወደ ነገድ ምንም አይተላለፍ፤ ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ወደ አባቶቹ ነገድ ርስት ይጠጋ።
8 ፤ ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ሰው የአባቶቹን ርስት ይወርስ ዘንድ፥ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ ርስት ያላት ሴት ልጅ ሁሉ ከአባትዋ ነገድ ባል ታግባ።
9 ፤ እንደዚህም ከአንድ ነገድ ወደ ሌላ ነገድ ምንም ርስት አይተላለፍ ከእስራኤልም ልጆች ነገድ እያንዳንዱ ወደ ርስቱ ይጠጋ።
10 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች አደረጉ።
11 ፤ የሰለጰዓድ ልጆች ማህለህ፥ ቲርጻ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ኑዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋር ተጋቡ።
12 ፤ ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ልጆች ወገኖች ባሎቻቸውን አገቡ፥ ርስታቸውም በአባታቸው ነገድ ጸና።
13 ፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የእስራኤልን ልጆች በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ ያዘዛቸው ትእዛዝና ፍርድ እነዚህ ናቸው።