ምዕራፍ 15

እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደምሰጣችሁ ወደ መኖሪያችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥
3 ፤ ስእለታችሁን ልትፈጽሙ፥ ወይም በፈቃዳችሁ፥ ወይም በበዓላችሁ፥ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ ታደርጉ ዘንድ ከበሬ ወይም ከበግ መንጋ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም መሥዋዕት የሚሆን የእሳት ቍርባን ለእግዚአብሔር ብታቀርቡ፥
4
5 ፤ ቍርባኑን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ከሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ከሌላ መሥዋዕት ጋር ለእያንዳንዱ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን፥ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ያዘጋጃል።
6
7 ፤ ለአንዱም አውራ በግ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የኢን መስፈሪያ ሢሶ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን ታዘጋጃለህ፤ የኢን መስፈሪያ ሢሶም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ታቀርባለህ።
8 ፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ወይም ስእለትን ለመፈጸም ወይም ለደኅንነት መሥዋዕት ወይፈንን ለእግዚአብሔር ብታዘጋጅ፥
9 ፤ ከወይፈኑ ጋር የኢን መስፈሪያ ግማሽ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን ታቀርባለህ።
10 ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት ለተደረገ ቍርባን፥ የኢን መስፈሪያ ግማሽ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን ታቀርባለ።
11 ፤ እንዲሁ ለእያንዳንዱ ወይፈን ወይም ለእያንዳንዱ አውራ በግ ወይም ለእያንዳንዱ ተባት የበግ ወይም የፍየል ጠቦት ይደረጋል።
12 ፤ እንዳዘጋጃችሁት ቍጥር፥ እንዲሁ እንደ ቍጥራቸው ለእያንዳንዱ ታደርጋላችሁ።
13 ፤ የአገር ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ቍርባን በእሳት ባቀረበ ጊዜ እንዲሁ ያደርጋል።
14 ፤ መጻተኛም ከእናንተ ጋር ቢቀመጥ፥ ወይም በትውልዳችሁ መካከል ማንም ሰው ቢኖር፥ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ቍርባን በእሳት ቢያቀርብ፥ እናንተ የምታደርጉትን እርሱ እንዲሁ ያደርጋል።
15 ፤ ለእናንተ በጉባኤው ላላችሁ በእናንተም መካከል ለሚቀመጥ መጻተኛ አንድ ሥርዓት ይሆናል፥ ለልጅ ልጃችሁም የዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤ እናንተ እንደ ሆናችሁ እንዲሁ በእግዚአብሔር ፊት መጻተኛ ይሆናል።
16 ፤ ለእናንተና ከእናንተ ጋር ለሚቀመጥ መጻተኛ አንድ ሕግና አንድ ፍርድ ይሆናል።
17 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
18 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደማመጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥
19 ፤ እናንተ የምድሪቱን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ታደርጋላችሁ።
20 ፤ መጀመሪያ ከምታደርጉት ሊጥ አንድ እንጐቻ ለማንሣት ቍርባን ታቀርባላችሁ፤ ከአውድማም እንደምታነሡት ቍርባን እንዲሁ ታነሣላችሁ።
21 ፤ መጀመሪያ ከምታደርጉት ሊጥ የማንሣት ቍርባን እስከ ልጅ ልጃችሁ ለእግዚአብሔር ትሰጣላችሁ።
22 ፤ ብትስቱም፥ እግዚአብሔርም ለሙሴ ያዘዛቸውን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥
23 ፤ እግዚአብሔር ካዘዘበት ከፊተኛው ቀን ጀምሮ ወደ ፊትም እስከ ልጅ ልጃችሁ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ያዘዛችሁን ሁሉ ባታደርጉ፥
24 ፤ ማኅበሩ ሳያውቁ በስሕተት ቢደረግ፥ ማኅበሩ ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከእህሉ ቍርባንና ከመጠጡ ቍርባን ጋር እንደ ሕጉ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን አንድ ወይፈን፥ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ያቀርባሉ።
25 ፤ ካህኑም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ያስተሰርይላቸዋል፥ ስሕተትም ነበረና ይሰረይላቸዋል፤ ስለ ስሕተታቸውም ለእግዚአብሔር ቍርባናቸውን በእሳት አቅርበዋል፥ ለእግዚአብሔርም የኃጢአታቸውን መሥዋዕት አቅርበዋል።
26 ፤ በሕዝቡም ሁሉ ዘንድ ያለ እውቀት ተደርጎአልና ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በመካከላቸውም ለሚኖሩት መጻተኞች ስርየት ይደረግላቸዋል።
27 ፤ አንድ ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ ለኃጢአት መሥዋዕት አንዲት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያቀርባል።
28 ፤ ኃጢአት ሠርቶ ሳያውቅ፥ ለሳተ ለዚያ ሰው ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፥ ይሰረይለትማል።
29 ፤ ትውልዱ በእስራኤል ልጆች መካከል ቢሆን፥ ወይም በመካከላቸው የሚቀመጥ መጻተኛ ቢሆን፥ ሳያውቅ ኃጢአትን ለሚሠራ ሁሉ ሕጉ አንድ ይሆንለታል።
30 ፤ የአገር ልጅ ቢሆን ወይም መጻተኛ ቢሆን፥ አንዳች በትዕቢት የሚያደርግ ሰው እግዚአብሔርን ሰድቦአል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል።
31 ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቀ፥ ትእዛዙንም ስለ ሰበረ፥ ያ ሰው ፈጽሞ ይጥፋ፤ ኃጢአቱ በራሱ ላይ ነው።
32 ፤ የእስራኤልም ልጆች በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም አገኙ።
33 ፤ እንጨትም ሲለቅም ያገኙት ሰዎች ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ ማኅበሩም ሁሉ አመጡት።
34 ፤ ያደርጉበትም ዘንድ የሚገባው አልተገለጠምና በግዞት አስቀመጡት።
35 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ሰውየው ፈጽሞ ይገደል፤ ከሰፈሩ ውጭ ማኅበሩ ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት አለው።
36 ፤ ማኅበሩም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አወጡት፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ወገሩት።
37 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
38 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው። እነርሱም ትውልዶቻቸውም በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ ያደርጉ ዘንድ፥ በዘርፉም ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል ያደርጉ ዘንድ እዘዛቸው።
39 ፤ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ እርስዋን በመከተል ያመነዘራችሁባትን የልባችሁንና የዓይኖቻችሁን ፈቃድ እንዳትከተሉ፥
40 ፤ ትእዛዜን ሁሉ ታስቡና ታደርጉ ዘንድ፥ ለአምላካችሁም ቅዱሳን ትሆኑ ዘንድ ዘርፉ በልብሳችሁ ላይ እንዲታይ ይሁን።
41 ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ አምላክ እሆናችሁ ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።