ምዕራፍ 23

በለዓምም ባላቅን። ሰባት መሠዊያ በዚህ ሥራልኝ፥ ሰባትም ወይፈን ሰባትም አውራ በግ በዚህ አዘጋጅልኝ አለው።
2 ፤ ባላቅም በለዓም እንደ ተናገረ አደረገ፤ ባላቅና በለዓምም በየመሠዊያው ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረጉ።
3 ፤ በለዓምም ባላቅን። በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ፥ እኔም እሄዳለሁ፤ ምናልባት እግዚአብሔር ሊገናኘኝ ይመጣል፤ እርሱም የሚገልጥልኝን እነግርሃለሁ አለው። ወደ ጉብታም ሄደ።
4 ፤ እግዚአብሔርም ከበለዓም ጋር ተገናኘ፤ እርሱም። ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጀሁ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረግሁ አለው።
5 ፤ እግዚአብሔርም ቃልን በበለዓም አፍ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው።
6 ፤ ወደ እርሱም ተመለሰ፥ እነሆም፥ እርሱና የሞዓብ አለቆች ሁሉ በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር።
7 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥እንዲህም አለ፦ ባላቅ ከአራም አመጣኝ፥ የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች፤ ና፥ ያዕቆብን ርገምልኝ፤ ና፥ እስራኤልን ተጣላልኝ ብሎ።
8 ፤ እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ? እግዚአብሔር ያልተጣላውን እንዴት እጣላለሁ?
9 ፤ በአምቦች ራስ ላይ ሆኜ አየዋለሁ፥ በኮረብቶችም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤ እነሆ፥ ብቻውን የሚቀመጥ ሕዝብ ነው፥ በአሕዛብም መካከል አይቈጠርም።
10 ፤ የያዕቆብን ትቢያ ማን ይቈጥራል? የእስራኤልስ እርቦ ማን ይቈጥራል? የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥ ፍጻሜዬም እንደ እርሱ ፍጻሜ ትሁን።
11 ፤ ባላቅም በለዓምን። ያደረግህብኝ ምንድር ነው? ጠላቶቼን ትረግምልኝ ዘንድ ጠራሁህ፤ እነሆም፥ ፈጽመህ ባረክሃቸው አለው።
12 ፤ እርሱም መልሶ። በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ አልጠነቀቅምን? አለው።
13 ፤ ባላቅም። በዚያ ሆነህ ታያቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ከእኔ ጋር ወደ ሌላ ቦታ ና ዳርቻቸውንም ብቻ ታያለህ፥ ሁሉን ግን አታይም፤ በዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ አለው።
14 ፤ ወደ ጾፊምም ሜዳ ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ ላይ ወሰደው፤ ሰባትም መሠዊያዎች ሠራ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈን አንድም አውራ በግ አሳረገ።
15 ፤ ባላቅንም። እኔ ወደዚያ ለመገናኘት ስሄድ በዚህ በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ አለው።
16 ፤ እግዚአብሔርም በለዓምን ተገናኘ፥ ቃልንም በአፉ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው።
17 ፤ ወደ እርሱም መጣ፥ እነሆም፥ እርሱ ከእርሱም ጋር የሞዓብ አለቆች በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር፤ ባላቅም። እግዚአብሔር የተናገረው ምንድር ነው? አለው።
18 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ። ባላቅ ሆይ፥ ተነሣ፥ ስማ፤ የሴፎር ልጅ ሆይ፥ አድምጠኝ፤
19 ፤ ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?
20 ፤ እነሆ፥ ለመባረክ ትእዛዝን ተቀብያለሁ፤ እርሱ ባርኮአል፥ እመልሰውም ዘንድ አልችልም።
21 ፤ በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፥ በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፤ አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፥ የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ።
22 ፤ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶአቸዋል፤ ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው።
23 ፤ በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥ በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤ በጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል። እግዚአብሔር ምን አደረገ! ይባላል።
24 ፤ እነሆ፥ ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይቆማል፥ እንደ አንበሳም ይነሣል፤ ያደነውን አስኪበላ፥ የገደለውንም ደሙን እስኪጠጣ አይተኛም።
25 ፤ ባላቅም በለዓምን። ከቶ አትርገማቸው፥ ከቶም አትባርካቸው አለው።
26 ፤ በለዓምም መልሶ ባላቅን። እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ አደርጋለሁ ብዬ አልተናገርሁህምን? አለው።
27 ፤ ባላቅም በለዓምን። ና፥ ወደ ሌላ ስፍራ እወስድሃለሁ፤ ምናልባት በዚህ ሆነህ እነርሱን ትረግምልኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይወድዳል አለው።
28 ፤ ባላቅም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፌጎር ላይ በለዓምን ወሰደው።
29 ፤ በለዓምም ባላቅን። በዚህ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፥ በዚህም ሰባት ወይፈን ሰባትም አውራ በግ አዘጋጅልኝ አለው።
30 ፤ ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረገ።