ምዕራፍ 35

እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2 ፤ ሌዋውያን የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ከርስታቸው ይሰጡ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፤ በከተሞቹም ዙሪያ ያለውን መሰምርያ ለሌዋውያን ስጡ።
3 ፤ እነርሱም በከተሞቹ ውስጥ ይቀመጣሉ፤ መሰምርያቸውም ለከብቶቻቸው ለእንስሶቻቸውም ለእነርሱም ላለው ሁሉ ይሁን።
4 ፤ ለሌዋውያንም የምትሰጡት የከተማ መሰምርያ በከተማው ዙሪያ ከቅጥሩ ወደ ውጭ አንድ ሺህ ክንድ ይሁን።
5 ፤ ከከተማው ውጭ በምሥራቅ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በደቡብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በምዕራብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በሰሜንም በኩል ሁለት ሺህ ክንድ ትከነዳላችሁ፥ ከተማውም በመካከል ይሆናል፤ ይህም የከተሞቹ መሰምርያ ይሆንላቸዋል።
6 ፤ ለሌዋውያንም የምትሰጡአቸው ስድስቱ የመማፀኛ ከተሞች ናቸው፤ እነርሱም ነፍሰ ገዳይ ይሸሽባቸው ዘንድ የምትሰጡአቸው ናቸው፤ ከእነዚህም ሌላ አርባ ሁለት ከተሞች ትሰጣላችሁ።
7 ፤ ለሌዋውያን የምትሰጡአቸው ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከመሰምርያቸው ጋር ትሰጡአቸዋላችሁ።
8 ፤ ከእስራኤል ልጆች ርስት ለሌዋውያን የምትሰጡአቸውን ከተሞች እንዲሁ ስጡ፤ ከብዙዎቹ ብዙ፥ ከጥቂቶቹ ጥቂት ትወስዳላችሁ፤ እያንዳንዱ እንደ ወረሱት እንደ ርስታቸው መጠን ከከተሞቻቸው ለሌዋውያን ይሰጣሉ።
9 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
10 ፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥
11 ፤ በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ ይሸሽ ዘንድ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ከተሞችን ለእናንት ለዩ።
12 ፤ ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹም ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ።
13 ፤ የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ።
14 ፤ በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፥ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ።
15 ፤ በስሕተት ነፍስ የገደለ ይሸሽበት ዘንድ እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ።
16 ፤ በብረት መሣርያ እስኪሞት ድረስ ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል።
17 ፤ ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው ድንጋይ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል።
18 ፤ ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው በእንጨት መሣርያ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል።
19 ፤ ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደል፤ ባገኘው ጊዜ ይግደለው።
20 ፤ እስኪሞት ድረስ በጥላቻ ቢደፋው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥
21 ፤ ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም ተበቃዩ ባገኘው ጊዜ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው።
22 ፤ ነገር ግን ያለ ጥላቻ ድንገት ቢደፋው፥ ሳይሸምቅም አንዳች ነገር ቢጥልበት፥
23 ፤ ወይም ሳያየው እስኪሞት ድረስ ሰው የሚሞትበትን ድንጋይ ቢጥልበት፥ ጠላቱም ባይሆን፥ ክፉም ያደርግበት ዘንድ ባይሻ፥
24 ፤ ማኅበሩ በመቺውና በደም ተባቃዩ መካከል ፍርድን እንደዚሁ ይፍረድ፤
25 ፤ ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ያድነዋል፥ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛ ከተማ ይመልሰዋል፤ በቅዱስ ዘይትም የተቀባው ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል።
26 ፤ ነፍሰ ገዳዩ ግን ከሸሸበት ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ቢወጣ፥
27 ፤ ደም ተበቃዩም ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ውጭ ቢያገኘው፥ ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው፥ የደም ዕዳ አይሆንበትም፤
28 ፤ ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረሰ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ዋነኛው ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል።
29 ፤ እነዚህም ነገሮች ለልጅ ልጃችሁ በማደሪያችሁ ሁሉ ሥርዓትና ፍርድ ይሁኑላችሁ።
30 ፤ ነፍሰ ገዳይ ሁሉ በምስክሮች አፍ ይገደላል፤ በአንድ ምስክር ግን ማናቸውንም ሰው መግደል አይገባም።
31 ፤ ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።
32 ፤ ዋነኛው ካህን ሳይሞት ወደ ምድሩ ይመለስ ዘንድ ወደ መማፀኛው ከተማ ከሸሸው የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ።
33 ፤ ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱአት፤ በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም።
34 ፤ እኔ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁና የምትኖሩባትን በመካከልዋም የማድርባትን ምድር አታርክሱአት።