ምዕራፍ 12

ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ በእርግጥ እናንተ ዓይነተኞች ሰዎች ናቸሁ፤ ጥበብም ከእናንተ ጋር ይሞታል።
3 ፤ ነገር ግን እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ማስተዋል አለኝ፤ ከእናንተም የማንስ አይደለሁም፤ እንደዚህ ያለውን ነገር የማያውቅ ማን ነው?
4 ፤ እግዚአብሔርን የጠራሁ እርሱም የመለሰልኝ እኔ ለባልንጀራው መሳለቂያ እንደሚሆን ሰው ሆኛለሁ፤ ጻድቅና ፍጹም ሰው መሳለቂያ ሆኖአል።
5 ፤ ተዘልሎ በሚቀመጥ ሰው አሳብ መከራ ይናቃል፤ ነገር ግን እግሩን ሊያድጠው ተዘጋጅቶአል።
6 ፤ የቀማኞች ድንኳን በደኅንነት ይኖራል፥ እግዚአብሔርንም የሚያስቈጡ ተዘልለው ተቀምጠዋል፤ እግዚአብሔር ሁሉን በእጃቸው አምጥቶላቸዋል።
7 ፤ አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፤ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።
8 ፤ ወይም ለምድር ተናገር፥ እርስዋም ታስተምርሃለች፤ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል።
9 ፤ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?
10 ፤ የሕያዋን ሁሉ ነፍስ የሰውም ሁሉ መንፈስ በእጁ ናት።
11 ፤ ምላስ መብልን እንደሚቀምስ፥ ጆሮ ቃልን የሚለይ አይደለምን?
12 ፤ በሽምግልና ጊዜ ጥበብ፥ በዘመንስ ርዝመት ማስተዋል ይገኛል።
13 ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ፤ ለእርሱ ምክርና ማስተዋል አለው።
14 ፤ እነሆ፥ ይፈርሳል፥ የፈረሰውም ተመልሶ አይሠራም፤ በሰውም ቢዘጋበት የሚከፍትለት የለም።
15 ፤ እነሆ፥ ውኆቹን ይከለክላል፥ እነርሱም ይደርቃሉ፤ እንደ ገና ይሰድዳቸዋል፥ ምድሪቱንም ይገለብጣሉ።
16 ፤ ኃይልና ጥበብ በእርሱ ዘንድ ናቸው፤ የሚስተውና የሚያስተው ለእርሱ ናቸው።
17 ፤ መካሮችንም እንደ ዘረፋ ይወስዳቸዋል፥ ፈራጆችንም ያሳብዳል።
18 ፤ የነገሥታትንም እስራት ይፈታል፥ ወገባቸውንም በመታጠቂያ ያስራቸዋል።
19 ፤ ካህናትን እንደ ዘረፋ ይወስዳቸዋል፥ ኃያላንንም ይገለብጣቸዋል።
20 ፤ ከታመኑ ሰዎችም ቋንቋን ያርቃል፥ የሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይወስድባቸዋል።
21 ፤ በአለቆች ላይ ንቀትን ያፈስሳል፥ የብርቱዎችንም መታጠቂያ ያላላል።
22 ፤ ጥልቅ ነገር ከጨለማ ይገልጣል፥ የሞትንም ጥላ ወደ ብርሃን ያወጣል።
23 ፤ አሕዛብን ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ እነርሱንም ያጠፋል፤ አሕዛብንም ያሰፋል፥ እነርሱንም ያፈልሳቸዋል።
24 ፤ ከምድር አሕዛብ አለቆች ዘንድ ማስተዋልን ይወስዳል፥ መንገድም በሌለበት በረሃ ያቅበዘብዛቸዋል።
25 ፤ ብርሃንም ሳይኖር በጨለማ ይርመሰመሳሉ፤ እንደ ሰካራም ይቅበዘበዛሉ።