ምዕራፍ 36

ኤሊሁም ደግሞ መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ ገና ስለ እግዚአብሔር የሚነገር አለኝና ጥቂት ቆየኝ፥ እኔም አስታውቅሃለሁ።
3 ፤ እውቀቴን ከሩቅ አመጣለሁ፥ ፈጣሪዬንም። ጻድቅ ነው እላለሁ።
4 ፤ ቃሌ በእውነት ያለ ሐሰት ነው፤ በእውቀትም ፍጹም የሆነ ከአንተ ጋር አለ።
5 ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም፤ እርሱም በማስተዋል ብርታት ኃያል ነው።
6 ፤ እርሱ የበደለኞችን ሕይወት አያድንም፤ ለችግረኞች ግን ፍርዱን ይሰጣል።
7 ፤ ዓይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም፤ ለዘላለምም ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፥ እነርሱም ከፍ ከፍ ይላሉ።
8 ፤ በሰንሰለት ቢታሰሩ፥ ወይም በችግር ገመድ ቢጠመዱ፥
9 ፤ ሥራቸውንና መተላለፋቸውን በትዕቢትም እንዳደረጉ ይናገራቸዋል።
10 ፤ ጆሮአቸውን ለተግሣጽ ይከፍተዋል፥ ከኃጢአትም ይመለሱ ዘንድ ያዝዛቸዋል።
11 ፤ ቢሰሙ ቢያገለግሉትም፥ ዕድሜአቸውን በልማት፥ ዘመናቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ።
12 ፤ ባይሰሙ ግን በሰይፍ ይጠፋሉ፥ ያለ እውቀትም ይሞታሉ።
13 ፤ ዝንጉዎች ግን ቍጣን ያዘጋጃሉ፤ እርሱም ባሰራቸው ጊዜ አይጮኹም።
14 ፤ በሕፃንነታቸው ሳሉ ይሞታሉ፥ ሕይወታቸውም በሰዶማውያን መካከል ይጠፋል።
15 ፤ የተቸገረውን በችግሩ ያድነዋል፤ በመከራም ጆሮአቸውን ይገልጣል።
16 ፤ እንዲሁም አንተን ከመከራ ችግር ወደሌለበት ወደ ሰፊ ስፍራ በወሰደህ ነበር፥ በማዕድህ ላይ የተዘጋጀውም ስብ በሞላበት ነበር።
17 ፤ አንተ ግን በበደለኞች ፍርድ የተሞላህ ነህ፤ ስለዚህ ፍርድና ብይን ይይዝሃል።
18 ፤ ቍጣ ለስድብ አያታልልህ፤ የማማለጃም ብዛት ፈቀቅ አያድርግህ።
19 ፤ ባለጠግነትህ የኃይልህም ብርታት ሁሉ ያለ ችግር እንድትሆን ሊረዳህ ይችላልን?
20 ፤ ወገኖች ከስፍራቸው የሚወጡበትን ሌሊት አትመኝ።
21 ፤ ከመከራ ይልቅ ይህን መርጠሃልና ኃጢአትን እንዳትመለከት ተጠንቀቅ።
22 ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይሉ ከፍ ያለውን ነገር ያደርጋል፤ እንደ እርሱስ ያለ አስተማሪ ማን ነው?
23 ፤ መንገዱን ማን አዘዘለት? ወይስ። ኃጢአትን ሠርተሃል የሚለው ማን ነው?
24 ፤ ሰዎች የዘመሩትን ሥራውን ታከብር ዘንድ አስብ።
25 ፤ ሰዎች ሁሉ ተመልክተውታል፤ ሰውም ከሩቅ ያየዋል።
26 ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም።
27 ፤ የውኃውን ነጠብጣብ ወደ ላይ ይስባል፥ ዝናብም ከጉም ይንጠባጠባል፤
28 ፤ ደመናት ያዘንባሉ፥ በሰዎችም ላይ በብዙ ያንጠባጥባሉ።
29 ፤ የደመናውንም መዘርጋት፥ የማደሪያውንም ነጐድጓድ የሚያስተውል ማን ነው?
30 ፤ እነሆ፥ በዙሪያው ብርሃኑን ይዘረጋል፤ የባሕሩንም ጥልቀት ይከድናል።
31 ፤ በእነዚህ በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ብዙም ምግብ ይሰጣል።
32 ፤ እጆቹን በብርሃን ይሰውራል፥ በጠላቱም ላይ ይወጣ ዘንድ ያዝዘዋል፤
33 ፤ የነጐድጓድ ድምፅ ስለ እርሱ ይናገራል፤ እንስሶችም ደግሞ ስለሚመጣው ውሽንፍር ይጮኻሉ።