ምዕራፍ 14

ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፥ መከራም ይሞላዋል።
2 ፤ እንደ አበባ ይወጣል፥ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላም ይሸሻል፥ እርሱም አይጸናም።
3 ፤ እንደዚህስ ባለ ሰው ላይ ዓይኖችህን ትከፍታለህን? ከአንተስ ጋር እኔን ወደ ፍርድ ታገባለህን?
4 ፤ ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ ማን ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም።
5 ፤ የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፥ የወሩም ቍጥር በአንተ ዘንድ ነው፥ እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረግህለት።
6 ፤ እንደ ምንደኛ ዕድሜው እስኪፈጸም ድረስ ያርፍ ዘንድ ከእርሱ ጥቂት ዘወር በል።
7 ፤ ዛፍ ቢቈረጥ ደግሞ ያቈጠቍጥ ዘንድ፥ ቅርንጫፉም እንዳያልቅ ተስፋ አለው።
8 ፤ ሥሩም በምድር ውስጥ ቢያረጅ፥ ግንዱም በመሬት ውስጥ ቢሞት፥
9 ፤ ከውኃ ሽታ የተነሣ ያቈጠቍጣል፤ እንደ አትክልት ቅርንጫፍ ያወጣል።
10 ፤ ሰው ግን ይሞትና ይጋደማል፤ ሰውም ነፍሱን ይሰጣል፥ እርሱስ ወዴት አለ?
11 ፤ ውኃ ከባሕር ውስጥ ያልቃል፤ ወንዙም ያንሳል ይደርቅማል።
12 ፤ ሰውም ተኝቶ አይነሣም፤ ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ ከእንቅልፉም አይነሣም።
13 ፤ በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ! ቍጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ! ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ!
14 ፤ በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? መለወጤ እስኪመጣ ድረስ፥ የሰልፌን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር።
15 ፤ በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፤ የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር።
16 ፤ አሁን ግን እርምጃዬን ቈጥረኸዋል፤ ኃጢአቴንም ትጠባበቃለህ።
17 ፤ መተላልፌ በከረጢት ውስጥ ታትሞአል፥ ኃጢአቴንም ለብጠህበታል።
18 ፤ ተራራ ሲወድቅ ይጠፋል፥ ዓለቱም ከስፍራው ይፈልሳል፤
19 ፤ ውኆች ድንጋዮቹን ይፍቃሉ፤ ፈሳሾቹም የምድሩን አፈር ይወስዳሉ፤ እንዲሁ የሰውን ተስፋ ታጠፋዋለህ።
20 ፤ ለዘላለም ታሸንፈዋለህ፥ እርሱም ያልፋል፤ ፊቱን ትለውጣለህ፥ እርሱንም ትሰድደዋለህ።
21 ፤ ልጆቹ ቢከብሩ አያውቅም፤ ቢዋረዱም አያይም።
22 ፤ ነገር ግን የገዛ ሥጋው ሕመም ብቻ ይሰማዋል፥ ለራሱም ብቻ ያለቅሳል። ች