ምዕራፍ 37

ስለዚህም ልቤ ተንቀጠቀጠ፥ ከስፍራውም ተንቀሳቀሰ።
2 ፤ የድምፁን መትመም ስሙ፥ ከአፉም የሚወጣውን ጕርምርምታ አድምጡ።
3 ፤ እርሱን ወደ ሰማያት ሁሉ ታች፥ ብርሃኑንም ወደ ምድር ዳርቻ ይሰድዳል።
4 ፤ በስተ ኋላው ድምፅ ይጮኻል፤ በግርማውም ድምፅ ያንጐደጕዳል፤ ድምፁም በተሰማ ጊዜ መብረቁን አይከለክልም።
5 ፤ እግዚአብሔር በድምፁ ድንቅኛ ያንጐደጕዳል፤ እኛም የማናስተውለውን ታላቅ ነገር ያደርጋል።
6 ፤ በረዶውንና ውሽንፍሩን ብርቱንም ዝናብ። በምድር ላይ ውደቁ ይላል።
7 ፤ ሰው ሁሉ ሥራውን ያውቅ ዘንድ የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል።
8 ፤ አውሬዎቹም ወደ ጫካው ይገባሉ፥ በዋሾቻቸውም ይቀመጣሉ።
9 ፤ ከተሰወረ ማደሪያውም ዐውሎ ነፋስ፥ ከሰሜንም ብርድ ይወጣል።
10 ፤ ከእግዚአብሔር እስትንፋስ ውርጭ ተሰጥቶአል፤ የውኆችም ስፋት ይጠብባል።
11 ፤ የውኃውንም ሙላት በደመና ላይ ይጭናል፤ የብርሃኑንም ደመና ይበታትናል፤
12
13 ፤ ለተግሣጽ ወይም ለምድሩ ወይም ለምሕረት ቢሆን፥ ሰው በሚኖርበት ዓለም ላይ ያዘዘውን ሁሉ ያደርግ ዘንድ ፈቃዱ ወደ መራችው ይዞራል።
14 ፤ ኢዮብ ሆይ፥ ይህን ስማ፤ ቁም፥ የእግዚአብሔርንም ተአምራት አስብ።
15 ፤ በውኑ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚያዝዛቸው፥ የደመናውንም ብርሃን እንዴት እንደሚያበራ አውቀሃልን?
16 ፤ ወይስ የደመናውን ሚዛን፥ ወይስ በእውቀት ፍጹም የሆነውን ተአምራት አውቀሃልን?
17 ፤ በደቡብ ነፋስ ምድር ጸጥ ባለች ጊዜ፥ ልብስህ የሞቀች አንተ ሆይ፥
18 ፤ እንደ ቀለጠ መስተዋት ብርቱ የሆኑትን ሰማያት ከእርሱ ጋር ልትዘረጋ ትችላለህን?
19 ፤ እኛ ከጨለማ የተነሣ በሥርዓት መናገር አንችልምና የምንለውን አስታውቀን።
20 ፤ ማንም በእርሱ ላይ ቢናገር ፈጽሞ ይዋጣልና እኔ እናገር ዘንድ ብወድድ ሰው ይነግረዋልን?
21 ፤ አሁንም ነፋስ አልፎ ካጠራቸው በኋላ፥ ሰው በሰማያት የሚበራውን ብርሃን ሊመለከት አይችልም።
22 ፤ ከሰሜን ወርቅ የሚመስል ጌጠኛ ብርሃን ይወጣል፤ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስፈራ ግርማ አለ።
23 ፤ ሁሉን የሚችል አምላክን እናገኝ ዘንድ አንችልም፤ በኃይል ታላቅ ነው፤ በፍርድና በጽድቅም አያስጨንቅም።
24 ፤ ስለዚህ ሰዎች ይፈሩታል፤ በልባቸውም ጠቢባን የሆኑትን ሁሉ አይመለከትም።