ምዕራፍ 20

ናዕማታዊውም ሶፋር መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ ስለዚህ በውስጤ ስላለው ችኰላ አሳቤ ትመልስልኛለች።
3 ፤ የሚያሳፍረኝንም ተግሣጽ ሰምቻለሁ፥ የማስተዋሌም መንፈስ ይመልስልኛል።
4 ፤ ሰው በምድር ላይ ከተቀመጠ፥ ከዱሮ ዘመን ጀምሮ፥
5 ፤ የኃጢአተኛ ፉከራ አጭር መሆኑን የዝንጉዎችም ደስታ ቅጽበት መሆኑን አታውቁምን?
6 ፤ ከፍታው ወደ ሰማይ ቢወጣ፥ ራሱም እስከ ደመና ቢደርስ፥
7 ፤ እንደ ፋንድያ ለዘላለም ይጠፋል፤ ያዩትም። ወዴት ነው? ይላሉ።
8 ፤ እንደ ሕልም ይበርራል፥ እርሱም አይገኝም፤ እንደ ሌሊትም ራእይ ይሰደዳል።
9 ፤ ያየችውም ዓይን ዳግመኛ አታየውም፤ ስፍራውም ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከተውም።
10 ፤ ልጆቹ ድሆቹን ያቈላምጣሉ፤ እጁ ሀብቱን ይመልሳል።
11 ፤ አጥንቶቹ ብላቴንነቱን ሞልተዋል፤ ነገር ግን ከእርሱ ጋር በመሬት ውስጥ ይተኛል።
12 ፤ ክፋት በአፉ ውስጥ ቢጣፍጥ፥ ከምላሱም በታች ቢሰውረው፥
13 ፤ ቢጠብቀውም ባይተወውም፥ በጕሮሮውም ቢይዘው፥
14 ፤ መብሉ በአንጀቱ ውስጥ ይገላበጣል፤ እንደ እፉኝትም ሐሞት በውስጡ ይሆናል።
15 ፤ የዋጠውን ሀብት ይተፋዋል፤ እግዚአብሔርም ከሆዱ ውስጥ ያወጣዋል።
16 ፤ የእፉኝትን መርዝ ይጠባል፤ የእባብም ምላስ ይገድለዋል።
17 ፤ የማሩንና የቅቤውን ፈሳሽ ወንዞቹንም አይመለከትም።
18 ፤ የድካሙን ፍሬ ሳይውጠው ይመልሰዋል፤ እንደ ንግዱም ትርፍ አይደሰትም።
19 ፤ ድሀውን አስጨንቆአል፥ ትቶታልም፤ ያልሠራውንም ቤት በዝብዞአል።
20 ፤ ሆዱ ዕረፍትን አላወቀምና የወደደው ነገር አላዳነውም።
21 ፤ እርሱ ከበላ በኋላ ምንም አልተረፈም፤ ስለዚህ በረከቱ አይከናወንለትም።
22 ፤ በጠገበ ጊዜ ይጨነቃል፤ የችግረኞችም ሁሉ እጅ ታገኘዋለች።
23 ፤ ሆዱን ሳያጠግብ እግዚአብሔር የቍጣውን ትኵሳት ይሰድድበታል፥ ሲበላም ያዘንብበታል።
24 ፤ ከብረት መሣርያም ይሸሻል፥ የናስም ቀስት ይወጋዋል።
25 ፤ እርሱም ይመዝዘዋል፥ ከሥጋውም ይወጣል፤ ከሐሞቱም ብልጭ ብሎ ይሠርጻል፤ ፍርሃትም ይወድቅበታል።
26 ፤ ጨለማ ሁሉ ስለ ከበረው ዕቃ ተዘጋጅቶአል፤ በሰው አፍ እፍ የማትባል እሳት ትበላዋለች፤ በድንኳኑ ውስጥ የቀረው ይጨነቅባታል።
27 ፤ ሰማይ ኃጢአቱን ይገልጥበታል፥ ምድርም ትነሣበታለች።
28 ፤ የቤቱም ባለጠግነት ይሄዳል፤ በቍጣው ቀን እንደ ፈሳሽ ውኃ ያልፋል።
29 ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የበደለኛ ሰው እድል ፈንታ፥ ከእግዚአብሔርም የተመደበ ርስቱ ይህ ነው።