ምዕራፍ 28

በእውነት ብር የሚወጣበት፥ ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ።
2 ፤ ብረት ከመሬት ውስጥ ይወሰዳል፤ መዳብም ከድንጋይ ይቀለጣል።
3 ፤ ሰው ለጨለማ ፍጻሜን ያደርጋል፤ የጨለማውንና የሞት ጥላን ድንጋይ እስከ ወሰኑ ድረስ ይፈላልጋል።
4 ፤ ሰው ከሚኖርበት ርቀው መውረጃ ይቈፍራሉ፤ ከሰውም እግር ተረሱ፥ ከሰዎችም ርቀው እየተንጠለጠሉ ይወዛወዛሉ።
5 ፤ እንጀራ ከምድር ውስጥ ይወጣል፤ በእሳትም እንደሚሆን ታችኛው ይገለበጣል።
6 ፤ ድንጋይዋ የሰንፔር ስፍራ ነው፥ የወርቅም ድቃቂ አለው።
7 ፤ መንገድዋን ጭልፊት አያውቀውም፥ የአሞራም ዓይን አላየውም።
8 ፤ የትዕቢት ልጆች አልረገጡአትም፥ ደቦል አንበሳ አላለፈባትም።
9 ፤ ሰው ወደ ቡላድ ድንጋይ እጁን ይዘረጋል፥ ተራራውንም ከመሠረቱ ይገለብጣል።
10 ፤ ከድንጋይ ውስጥ መንዶልዶያ ይወቅራል፤ ዓይኑም ዕንቍን ሁሉ ታያለች።
11 ፤ ፈሳሹም እንዳይንጠባጠብ ይገድባል፤ የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል።
12 ፤ ነገር ግን ጥበብ የምትገኘው ወዴት ነው? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?
13 ፤ ሰው መንገድዋን አያውቅም፤ በሕያዋን ምድር አትገኝም።
14 ፤ ቀላይ። በእኔ ውስጥ የለችም ይላል፤ ባሕርም። በእኔ ዘንድ የለችም ይላል።
15 ፤ በምዝምዝ ወርቅ አትገኝም፥ ብርም ስለ ዋጋዋ አይመዘንም።
16 ፤ በኦፊር ወርቅ፥ በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም።
17 ፤ ወርቅና ብርጭቆ አይወዳደሩአትም፥ በጥሩ ወርቅም ዕቃ አትለወጥም።
18 ፤ ስለ ዛጐልና ስለ አልማዝ አይነገርም። የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቍ ይልቅ ይበልጣል።
19 ፤ የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን አይተካከላትም፥ በጥሩም ወርቅ አትገመትም።
20 ፤ እንግዲያሳ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?
21 ፤ ከሕያዋን ሁሉ ዓይን ተሰውራለች፥ ከሰማይ ወፎች ተሸሽጋለች።
22 ፤ ጥፋትና ሞት። ወሬዋን በጆሮቻችን ሰማን ብለዋል።
23 ፤ እግዚአብሔር መንገድዋን ያስተውላል፥ እርሱም ስፍራዋን ያውቃል።
24 ፤ እርሱም የምድርን ዳርቻ ይመለከታል፥ ከሰማይም በታች ያለውን ሁሉ ያያል።
25 ፤ ለነፋስ ሚዛንን ባደረገለት ጊዜ፥ ውኆችንም በስፍር በሰፈረ ጊዜ፥
26 ፤ ለዝናብም ሥርዓትን፥ ለነጐድጓድ መብረቅም መንገድን ባደረገ ጊዜ፥
27 ፤ በዚያን ጊዜ አያት፥ ገለጣትም፤ አዘጋጃትም፥ ደግሞም መረመራት።
28 ፤ ሰውንም። እነሆ፥ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከኃጢአትም መራቅ ማስተዋል ነው አለው።