ምዕራፍ 35

ኤሊሁም ደግሞ መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ ይህ ጽድቅ እንደ ሆነ ታስባለህን? ወይስ። በእግዚአብሔር ፊት እኔ ጻድቅ ነኝ ትላለህን?
3 ፤ አንተ። ምን ጥቅም አለህ? ኃጢአት ሠርቼ ከማገኘው ይልቅ ኃጢአት ባልሠራ ኖሮ ምን እጠቀማለሁ? ብለህ ጠይቀሃልና።
4 ፤ እኔ ለአንተና ከአንተ ጋር ላሉ ለባልንጀሮችህ እመልሳለሁ።
5 ፤ ዓይኖችህን ወደ ሰማይ አቅንተህ እይ፤ ከአንተም ከፍ ከፍ ያሉትን ደመናት ተመልከት።
6 ፤ ኃጢአት ብትሠራ ምን ትጐዳዋለህ? መተላለፍህስ ቢበዛ ምን ታደርገዋለህ?
7 ፤ ጻድቅስ ብትሆን ምን ትሰጠዋለህ? ወይስ ከእጅህ ምንን ይቀበላል?
8 ፤ እንደ አንተ ያለውን ሰው ክፋትህ ይጐዳዋል፤ ለሰውም ልጅ ጽድቅህ ይጠቅመዋል።
9 ፤ ከግፍ ብዛት የተነሣ ሰዎች ይጮኻሉ፤ ከኃያላንም ክንድ የተነሣ ለእርዳታ ይጠራሉ።
10
11 ፤ ነገር ግን። በሌሊት መዝሙርን የሚሰጥ፥ ከምድርም እንስሶች ይልቅ የሚያስተምረን ከሰማይም ወፎች ይልቅ ጥበበኞች የሚያደርገን፤ ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ወዴት ነው? የሚል የለም።
12 ፤ በዚያ ስለ ክፉ ሰዎች ትዕቢት ይጮኻሉ፥ እርሱ ግን አይመልስላቸውም።
13 ፤ በእውነት እግዚአብሔር ከንቱ ነገርን አይሰማም፥ ሁሉን የሚችል አምላክም አይመለከተውም፤
14 ፤ ይልቁንም። አላየውም፤ ነገሩ በእርሱ ፊት ነው፥ እኔም አጠብቀዋለሁ ስትል።
15 ፤ አሁን ግን በቍጣው አልጐበኘምና። በኃጢአት እጅግ አያስብም ትላለህ።
16 ፤ ስለዚህ ኢዮብ አፉን በከንቱ ይከፍታል፥ ያለ እውቀትም ቃሉን ያበዛል።