ምዕራፍ 8

ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ እስከ መቼ ይህን ትናገራለህ? የአፍህስ ቃል እስከ መቼ እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናል?
3 ፤ በውኑ እግዚአብሔር ፍርድን ያጣምማልን? ሁሉንም የሚችል አምላክ ጽድቅን ያጣምማልን?
4 ፤ ልጆችህ በድለውት እንደ ሆነ፥ እርሱ በበደላቸው እጅ ጥሎአቸዋል።
5 ፤ እግዚአብሔርን ብትገሠግሥ፥ ሁሉንም የሚችለውን አምላክ ብትለምን፥
6 ፤ ንጹሕና ቅን ብትሆን፥ በእውነት አሁን ስለ አንተ ይነቃል፥ የጽድቅህንም መኖሪያ ያከናውንልሃል።
7 ፤ ጅማሬህ ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍጻሜህ እጅግ ይበዛል።
8
9 ፤ ዘመናችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ነውና እኛ የትናንት ብቻ ነን፤ ምንም አናውቅም፤ ስለዚህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፥ አባቶቻቸውም ለመረመሩት ነገር ትጋ፤
10 ፤ እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፥ ቃልንም ከልባቸው የሚያወጡ አይደሉምን?
11 ፤ በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጠማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማልን?
12 ፤ ገና ሲለመልም ሳይቈረጥም፥ ከአትክልት ሁሉ በፊት ይደርቃል።
13 ፤ እግዚአብሔርን የሚረሱ ሁሉ ፍጻሜአቸው እንዲሁ ነው፤ የዝንጉም ሰው ተስፋ ይጠፋል።
14 ፤ ተስፋው ይቈረጣል፥ እምነቱም እንደ ሸረሪት ቤት ይሆናል።
15 ፤ ቤቱን ይደግፈዋል፥ አይቆምለትም፤ ይይዘውማል፥ አይጸናለትም።
16 ፤ ፀሐይም ሳይተኵስ ይለመልማል፥ ጫፉም በአታክልቱ ቦታ ይወጣል።
17 ፤ በድንጋይ ክምር ላይ ሥሩ ይጠመጠማል፤ የድንጋዮቹን ቦታ ይመለከታል።
18 ፤ ከቦታው ቢጠፋ። አላየሁህም ብሎ ይክደዋል።
19 ፤ እነሆ፥ የመንገዱ ደስታ እንዲህ ነው፤ ሌሎችም ከመሬት ይበቅላሉ።
20 ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር ፍጹሙን ሰው አይጥለውም፥ የኃጢአተኞችንም እጅ አያበረታም።
21 ፤ አፍህን እንደ ገና ሳቅ ይሞላል፥ ከንፈሮችህንም እልልታ ይሞላል።
22 ፤ የሚጠሉህ እፍረት ይለብሳሉ፤ የኃጢአተኞችም ድንኳን አይገኝም።