ምዕራፍ 2

ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣን ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም በመካከላቸው መጣ።
2 ፤ እግዚአብሔርም ሰይጣንን። ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። በምድር ላይ ዞርሁ፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ።
3 ፤ እግዚአብሔርም ሰይጣንን። በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም፤ በከንቱም አጠፋው ዘንድ አንተ በእርሱ ላይ ምንም ብታንቀሳቅሰኝ፥ እስከ አሁን ፍጹምነቱን ይዞአል።
4 ፤ ሰይጣንም መልሶ እግዚአብሔርን። ቁርበት ስለ ቁርበት ነው፤ ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል።
5 ፤ ነገር ግን አሁን እጅህን ዘርግተህ አጥንቱንና ሥጋውን ዳብስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል አለው።
6 ፤ እግዚአብሔም ሰይጣንን። ሕይወቱን ተወው እንጂ እነሆ፥ እርሱ በእጅህ ነው አለው።
7 ፤ ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፥ ኢዮብንም ከእግሩ ጫማ ጀምሮ እስከ አናቱ ድረስ በክፉ ቍስል መታው።
8 ፤ ሥጋውንም ይፍቅበት ዘንድ ገል ወሰደ፥ በአመድም ላይ ተቀመጠ።
9 ፤ ሚስቱም። እስከ አሁን ፍጹምነትህን ይዘሃልን? እግዚአብሔርን ስደብና ሙት አለችው። (የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው) ዳግመኛ እግዚአብሔርን ጥቂት ወራት ደጅ እጠናዋለሁ፤ ዳግመኛም መከራውን እታገሠዋለሁ፥ የቀድሞ ኑሮዬንም ተስፋ አደርገዋለሁ ትላለህን? አለችው። እንደዚህሳ እንዳትል ከዚህ ዓለም እነሆ ስም አጠራርህ ጠፋ፤ ሴቶች ልጆቼና ወንዶች ልጆቼም ሞቱ እኔስ ዘጠኝ ወር ሳረግዝ ሳምጥ ስወልድ ሳይረቡኝ ሳይጠቅሙኝ በከንቱ ደከምሁ አለች። አንተም በመግል ተውጠህ በትል ተከብበህ ትኖራለህ፤ ሌሊቱን ሁሉ ስትዛብር ታድራለህ። እኔ ግን እየዞርሁ እቀላውጣለሁ። ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እሄዳለሁ፤ ከድካሜ በእኔ ላይ ካለ ከችግሬም አርፍ ዘንድ ከጧት ጀምሮ ፀሐይ እስኪገባ ድረስ እጠብቃለሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔርን የማይገባ ቃል ተናግረኸው ሙት አለች።
10 ፤ እርሱ ግን አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን? አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።
11 ፤ ሦስቱም የኢዮብ ወዳጆች ይህን የደረሰበትን ክፉ ነገር ሁሉ ሰምተው ከየአገራቸው መጡ፤ እነርሱም ቴማናዊው ኤልፋዝ፥ ሹሐዊው በልዳዶስ፥ ነዕማታዊው ሶፋር ነበሩ። እነርሱም ሊያዝኑለትና ሊያጽናኑት በአንድነት ወደ እርሱ ለመምጣት ተስማሙ።
12 ፤ ከሩቅም ሆነው ዓይናቸውን ባነሡ ጊዜ አላወቁትም፤ ድምፃቸውንም አሰምተው አለቀሱ፤ እያንዳንዳቸውም መጐናጸፊያቸውን ቀደዱ፥ ወደ ላይም ወደ ራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ።
13 ፤ ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊትም ከእርሱ ጋር በምድር ላይ ተቀመጡ፤ ሕመሙም እጅግ እንደ በዛ አይተዋልና ከእነርሱ አንድ ቃል የሚናገረው አልነበረም።