ምዕራፍ 31

ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤ እንግዲህስ ቈንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ?
2 ፤ የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ከላይ፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ርስት ከአርያም ምንድር ነው?
3 ፤ መዓትስ ለኃጢአተኛ፥ መለየትስ ለሚበድሉ አይደለምችን?
4 ፤ መንገዴን አያይምን? እርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን?
5
6 ፤ በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፥ እግዚአብሔርም ቅንነቴን ይወቅ። በሐሰት ሄጄ እንደ ሆነ እግሬም ለሽንገላ ቸኵላ እንደ ሆነ፥
7 ፤ እርምጃዬ ከመንገድ ፈቀቅ ብሎ፥ ልቤም ዓይኔን ተከትሎ፥ ነውርም ከእጄ ጋር ተጣብቆ እንደ ሆነ፥
8 ፤ እኔ ልዝራ፥ ሌላ ሰውም ይብላው፤ የሚበቅለውም ሁሉ ይነቀል።
9 ፤ ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጐምጅቶ እንደ ሆነ፥ በባልንጀራዬም ደጅ አድብቼ እንደ ሆነ፥
10 ፤ ሚስቴ ለሌላ ሰው ትፍጭ፥ ሌሎችም በእርስዋ ላይ ይጐንበሱ።
11 ፤ ይህ ክፉ አበሳ፥ ፈራጆችም የሚቀጡበት በደል ነውና፤
12 ፤ ይህ እስከ ጥፋት ድረስ የሚበላ እሳት፥ ቡቃያዬንም ሁሉ የሚነቅል ነውና።
13 ፤ ወንድ ባሪያዬ ወይም ሴት ባሪያዬ ከእኔ ጋር በተምዋገቱ ጊዜ፥ ሙግታቸውን ንቄ እንደ ሆነ፥
14 ፤ እግዚአብሔር በተነሣ ጊዜ ምን አደርጋለሁ? በጐበኘኝ ጊዜ ምን እመልስለታለሁ?
15 ፤ እኔን በማኅፀን የፈጠረ እርሱንስ የፈጠረው አይደለምን? በማኅፀንስ ውስጥ የሠራን አንድ አይደለንምን?
16 ፤ ድሀውን ከልመናው ከልክዬ፥ የመበለቲቱን ዓይን አጨልሜ እንደ ሆነ፥
17 ፤ እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደ ሆነ፥ ድሀ አደጉም ደግሞ ከእርሱ ሳይበላ ቀርቶ እንደ ሆነ፤
18 ፤ እርሱን ግን ከታናሽነቴ ጀምሬ እንደ አባቱ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፥ እርስዋንም ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ መራኋት፤
19 ፤ ራቁቱን የሆነው ሰው ሲጠፋ፥ ወይም ድሀ ያለ ልብስ ሲሆን አይቼ እንደ ሆነ፥
20 ፤ ጐንና ጐኑ ያልባረከችኝ፥ በበጎቼም ጠጕር ያልሞቀ እንደ ሆነ፤
21 ፤ በበሩ ረዳት ስላየሁ፥ በድሀ አደጉ ላይ እጄን አንሥቼ እንደ ሆነ፥
22 ፤ ትከሻዬ ከመሠረትዋ ትውደቅ፥ ክንዴም ከመገናኛዋ ትሰበር።
23 ፤ የእግዚአብሔር መዓት አስደንግጦኛልና፤ በክብሩም ፊት ምንም ለማድረግ አልቻልሁም።
24 ፤ ወርቅን ተስፋ አድርጌ፥ ጥሩውንም ወርቅ። በአንተ እታመናለሁ ብዬ እንደ ሆነ፤
25 ፤ ሀብቴ ስለ በዛ፥ እጄም ብዙ ስላገኘች ደስ ብሎኝ እንደ ሆነ፤
26 ፤ ፀሐይ ሲበራ ጨረቃ በክብር ስትሄድ አይቼ፥
27 ፤ ልቤ በስውር ተታልሎ፥ አፌም እጄን ስሞ እንደ ሆነ፤
28 ፤ ልዑል እግዚአብሔርን በካድሁ ነበርና ይህ ደግሞ ፈራጆች የሚቀጡበት በደል በሆነ ነበር።
29 ፤ በሚጠላኝ መጥፋት ደስ ብሎኝ ክፉ ነገርም ባገኘው ጊዜ ሐሤት አድርጌ እንደ ሆነ፤
30 ፤ ነገር ግን በመርገም ነፍሱን በመሻት አንደበቴን ኃጢአት ይሠራ ዘንድ አልሰጠሁም፤
31 ፤ በድንኳኔ የሚኖሩ ሰዎች። በከብቱ ሥጋ ያልጠገበ ማን ይገኛል? ብለው እንደ ሆነ፤
32 ፤ መጻተኛው ግን በሜዳ አያድርም ነበር፥ ደጄንም ለመንገደኛ እከፍት ነበር፤
33 ፤ በደሌንም በብብቴ በመሸሸግ ኃጢአቴን እንደ ሰው ሰውሬ እንደ ሆነ፤
34 ፤ ከሕዝብ ብዛት ፈርቼ፥ የዘመዶቼም ንቀት አስደንግጦኝ፥ ዝም ብዬ ከደጅ ያልወጣሁ እንደ ሆነ፤
35 ፤ የሚያዳምጠኝ ምነው በኖረልኝ! እነሆ የእጄ ምልክት ሁሉን የሚችል አምላክ ይመልስልኝ፤ ከባላጋራዬ የተጻፈው የክስ ጽሑፍ ምነው በተገኘልኝ!
36 ፤ በትከሻዬ ላይ እሸከመው፥ አክሊልም አድርጌ በራሴ አስረው ነበር፤
37 ፤ የእርምጃዬን ቍጥር አስታውቀው፥ እንደ አለቃም ሆኜ አቀርብለት ነበር።
38 ፤ እርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ እንደ ሆነ፥ ትልሞችዋም በአንድ ላይ አልቅሰው እንደ ሆነ፤
39 ፤ ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ፥ የባለቤቶችንም ነፍስ አሳዝኜ እንደ ሆነ፥
40 ፤ በስንዴ ፋንታ አሜከላ፥ በገብስም ፋንታ ኵርንችት ይውጣብኝ። የኢዮብ ቃል ተፈጸመ።