ምዕራፍ 19

ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ ነፍሴን የምትነዘንዙ፥ በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው?
3 ፤ ይኸው ስትሰድቡኝ አሥር ጊዜ ነው፤ ስታሻክሩኝም አላፈራችሁም።
4 ፤ በእውነትም የሳትሁ እንደ ሆነ፥ ስሕተቴ ከእኔ ጋር ትኖራለች።
5 ፤ በእውነትም ብትጓደዱብኝ፥ መዋረዴን በእኔ ላይ ብትከራከሩ፥
6 ፤ እንግዲህ እግዚአብሔር እንደ ገለበጠኝ፥ በመረቡም እንደ ከበበኝ እወቁ።
7 ፤ እነሆ፥ ስለ ተደረገብኝ ግፍ ብጮኽ ማንም አይመልስልኝም፤ አሰምቼም ብጠራ ፍርድ የለኝም።
8 ፤ እንዳላልፍ መንገዴን ዘግቶታል፥ በጎዳናዬም ጨለማ አኑሮበታል።
9 ፤ ክብሬን ገፈፈኝ፥ ዘውዴንም ከራሴ ላይ ወሰደ።
10 ፤ በዚህና በዚያም አፈረሰኝ፥ እኔም ሄድሁ፤ ተስፋዬንም እንደ ዛፍ ነቀለው፤
11 ፤ ቍጣውንም አነደደብኝ፥ እንደ ጠላቱም ቈጠረኝ።
12 ፤ ሠራዊቱ አብረው መጡ፥ መንገዳቸውንም በላዬ አዘጋጁ፥ በድንኳኔም ዙሪያ ሰፈሩ።
13 ፤ ወንድሞቼን ከእኔ ዘንድ አራቀ፥ የሚያውቁኝም አጥብቀው ተለዩኝ።
14 ፤ ዘመዶቼ ተቋረጡ፥ ወዳጆቼም ረሱኝ።
15 ፤ ቤተ ሰቦቼና ሴቶች ባሪያዎቼ እንደ መጻተኛ ቈጠሩኝ፤ በዓይናቸውም እንደ እንግዳ ሆንሁ።
16 ፤ ባሪያዬን ብጠራ፥ በአፌም ባቈላምጥ አይመልስልኝም።
17 ፤ ሚስቴ እስትንፋሴን ጠላች፥ የእናቴም ማኅፀን ልጆች ልመናዬን ጠሉ።
18 ፤ ሕፃናቶች እንኳ አጠቁኝ፤ ብነሣም በእኔ ላይ ይናገራሉ።
19 ፤ አማካሪዎቼ ሁሉ ተጸየፉኝ፤ እኔ የምወድዳቸው በላዬ ተገለበጡ።
20 ፤ አጥንቴ ከቁርበቴና ከሥጋዬ ጋር ተጣበቀ፤ ድድ ብቻ ቀርቶልኝ አመለጥሁ።
21 ፤ እናንተ ወዳጆቼ ሆይ፥ ማሩኝ፤ የእግዚአብሔር እጅ መትታኛለችና ማሩኝ።
22 ፤ ስለ ምን እናንተ እንደ እግዚአብሔር ታሳድዱኛላችሁ? ከሥጋዬስ ስለ ምን አትጠግቡም?
23 ፤ ምነው አሁን ቃሌ ቢጻፍ! ምነው በመጽሐፍ ውስጥ ቢታተም!
24 ፤ ምነው በብረት ብርና በእርሳስ በዓለቱ ላይ ለዘላለም ቢቀረጽ!
25 ፤ እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥
26 ፤ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ።
27 ፤ እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል።
28 ፤ በእውነት። እንዴት እናሳድደዋለን? የነገሩ ሥር በእርሱ ዘንድ ተገኝቶአል ብትሉ፥
29 ፤ ፍርድ እንዳለ ታውቁ ዘንድ ቍጣ የሰይፍን ቅጣት ያመጣልና ከሰይፍ ፍሩ።