ምዕራፍ 23

ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ ዛሬም ደግሞ የኅዘን እንጕርጕሮዬ ገና መራራ ነው፤ እጁ በልቅሶ ጩኸቴ ላይ ከብዳለች።
3 ፤ እርሱን ወዴት እንዳገኘው ምነው ባወቅሁ! ወደ ተቀመጠበትስ ስፍራ ምነው በደረስሁ!
4 ፤ በፊቱ ሙግቴን አዘጋጅ ነበር፥ አፌንም በማስረጃ እሞላው ነበር።
5 ፤ የሚመልስልኝም ቃል ምን እንደ ሆነ አውቅ ነበር፥ የሚለኝንም አስተውል ነበር።
6 ፤ በኃይሉ ብዛት ከእኔ ጋር ይምዋገት ነበርን? እንኳን! ያደምጠኝ ነበር።
7 ፤ ቅን ሰው ከእርሱ ጋር በዚያ ይከራከር ነበር፤ እኔም ከፈራጄ ለዘላለም እድን ነበር።
8 ፤ እነሆ፥ ወደ ፊት እሄዳለሁ፥ እርሱም የለም፤ ወደ ኋላም እሄዳለሁ፥ እኔም አላስተውለውም፤
9 ፤ ወደሚሠራበት ወደ ግራ ብሄድ አልመለከተውም፤ በቀኜም ይሰወራል፥ አላየውምም፤
10 ፤ የምሄድበትን መንገድ ያውቃል፤ ከፈተነኝም በኋላ እንደ ወርቅ እወጣለሁ።
11 ፤ እግሬ ወደ እርምጃው ተጣብቆአል፤ መንገዱንም ጠብቄአለሁ፥ ፈቀቅም አላልሁም።
12 ፤ ከከንፈሩ ትእዛዝ አልተመለስሁም፤ የአፉን ቃል በልቤ ሰውሬአለሁ።
13 ፤ እርሱ ግን ብቻውን ነው፤ እርሱንስ የሚመስለው ማን ነው? ነፍሱም የወደደችውን ያደርጋል።
14 ፤ በእኔ ላይ የተወሰነውን ይፈጽማል፤ እንደዚህም ያለ ብዙ ነገር በእርሱ ዘንድ አለ።
15 ፤ ስለዚህ በፊቱ ደነገጥሁ፤ ባሰብሁም ጊዜ ከእርሱ ፈራሁ።
16 ፤ እግዚአብሔር ልቤን አባብቶታልና፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስደንግጦኛል።
17 ፤ ከጨለማው የተነሣ፥ ድቅድቁም ጨለማ ፊቴን ከመክደኑ የተነሣ አልደነገጥሁም።