ምዕራፍ 26

ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ ኃይል የሌለውን ምንኛ ረዳኸው! ብርታት የሌለውን ክንድ ምንኛ አዳንኸው!
3 ፤ ጥበብስ የሌለውን ምንኛ መከርኸው! ብዙ እውቀትንስ ምንኛ ገለጥህለት!
4 ፤ ይህንስ ቃል በማን እርዳታ ተናገርህ? የማንስ መንፈስ ከአንተ ዘንድ ወጣ?
5 ፤ ሙታን ሰዎች ከውኆች በታች፥ በውኆችም ውስጥ ከሚኖሩ በታች ይንቀጠቀጣሉ።
6 ፤ ሲኦል በፊቱ ራቁትዋን ናት፥ ለጥፋትም መጋረጃ የለውም።
7 ፤ ሰሜንን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል፥ ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል።
8 ፤ ውኆችን በደመናዎቹ ውስጥ ያስራል፥ ደመናይቱም ከታች አልተቀደደችም።
9 ፤ የዙፋኑን ፊት ይከድናል፥ ደመናውንም ይዘረጋበታል።
10 ፤ ብርሃንና ጨለማ እስከሚለያዩበት ዳርቻ ድረስ፥ በውኆች ፊት ላይ ድንበርን አደረገ።
11 ፤ የሰማይ አዕማድ ይንቀጠቀጣሉ፥ ከተግሣጹም የተነሣ ይደነግጣሉ።
12 ፤ በኃይሉ ባሕርን ጸጥ ያደርጋል፥ በማስተዋሉም ረዓብን ይመታል።
13 ፤ በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ፥ እጁም በራሪይቱን እባብ ወጋች።
14 ፤ እነሆ፥ ይህ የመንገዱ ዳርቻ ብቻ ነው፤ ይህም የሰማነው ነገር ምንኛ ጥቂት ነው! የኃይሉንስ ነጐድጓድ ያስተውል ዘንድ ማን ይችላል?