ምዕራፍ 27

ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ፥ እንዲህም አለ።
2 ፤ ፍርዴን ያስወገደ ሕያው እግዚአብሔርን! ነፍሴንም መራራ ያደረገ ሁሉን የሚችል ሕያው አምላክን!
3 ፤ እስትንፋሴ በእኔ ውስጥ፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በአፍንጫዬ ውስጥ ገና ሳለ፥
4 ፤ ከንፈሬ ኃጢአትን አትናገርም፥ አንደበቴም ሽንገላን አያወጣም።
5 ፤ እናንተን ማጽደቅ ከእኔ ዘንድ ይራቅ፤ እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅም።
6 ፤ ጽድቄን እይዛለሁ እርሱንም አልተውም፤ ከቀኖቼም ሁሉ ስለ አንዱ ልቤ አይዘልፈኝም።
7 ፤ ጠላቴ እንደ በደለኛ፥ በእኔ ላይም የሚነሣ እንደ ኃጢአተኛ ይሁን።
8 ፤ እግዚአብሔር ባጠፋውና ነፍሱን በለየ ጊዜ፥ የዝንጉ ሰው ተስፋው ምንድር ነው?
9 ፤ በውኑ መከራ በመጣበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ጩኸቱን ይሰማልን?
10 ፤ ሁሉንስ በሚችል አምላክ ደስ ይለዋልን? እግዚአብሔርንስ ሁልጊዜ ይጠራልን?
11 ፤ እኔ ስለ እግዚአብሔር እጅ አስተምራችኋለሁ፤ ሁሉን በሚችል አምላክ ዘንድ ያለውን አልሸሽግም።
12 ፤ እነሆ፥ ሁላችሁ አይታችኋል፤ ስለ ምን ከንቱ ሆናችሁ?
13 ፤ ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ የበደለኛ እድል ፈንታ፥ ግፈኛም ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ የሚቀበላት ርስት ናት፤
14 ፤ ልጆቹ ቢበዙ ለሰይፍ ይሆናሉ፤ ዘሩም እንጀራን አይጠግብም።
15 ፤ ለእርሱም የቀሩት በቸነፈር ይቀበራሉ፤ መበለቶቻቸውም አያለቅሱም።
16 ፤ እርሱ ብርን እንደ አፈር ቢከምር፥ ልብስንም እንደ ጭቃ ቢያዘጋጅ፥
17 ፤ እርሱ ያዘጋጀው ይሆናል፥ ነገር ግን ጻድቅ ይለብሰዋል፤ ብሩንም ንጹሐን ይከፋፈሉታል።
18 ፤ የሚሠራው ቤት እንደ ሸረሪት ድር ይሠራል፥ ጠባቂም እንደሚሠራው ጎጆ ነው።
19 ፤ ባለጠጋ ሆኖ ይተኛል፥ ዳግመኛም አይተኛም፤ ዓይኑን ይከፍታል፥ እርሱም የለም።
20 ፤ ድንጋጤ እንደ ጐርፍ ታገኘዋለች፤ በሌሊትም ዐውሎ ነፋስ ትነጥቀዋለች።
21 ፤ የምሥራቅ ነፋስ ያነሣዋል፥ እርሱም ይሄዳል፤ ከቦታውም ይጠርገዋል።
22 ፤ እርሱ ይጥልበታል፥ አይራራለትም፤ ከእጁ ፈጥኖ መሸሽ ይወድዳል።
23 ፤ ሰው በእጁ ያጨበጭብበታል፤ ከስፍራውም በፉጨት ያስወጡታል።