ምዕራፍ 29

ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ፥ እንዲህም አለ።
2 ፤ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደ ነበረው ጊዜ፥ እንደ ፊተኛው ወራት ምነው በሆንሁ!
3 ፤ በራሴ ላይ መብራቱ በበራ ጊዜ፥ እኔም ጨለማውን አልፌ በብርሃኑ በሄድሁ ጊዜ፥
4 ፤ በሙሉ ሰውነቴ እንደ ነበርሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ድንኳኔን በጋረደ ጊዜ፥
5 ፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ከእኔ ጋር ገና ሳለ፥ ልጆቼም በዙሪያዬ ሳሉ፥
6 ፤ መንገዴ በቅቤ ይታጠብ በነበረ ጊዜ፥ ድንጋዩ የዘይት ፈሳሽ ያፈስስልኝ በነበረ ጊዜ።
7 ፤ ወደ ከተማይቱ በር በወጣሁ ጊዜ፥ በአደባባዩም ወንበሬን ባኖርሁ ጊዜ፥
8 ፤ ጐበዛዝት እኔን አይተው ተሸሸጉ፥ ሽማግሌዎችም ተነሥተው ቆሙ።
9 ፤ አለቆቹ ከመናገር ዝም አሉ፥ እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ጫኑ።
10 ፤ የታላላቆቹም ድምፅ አረመመ፤ ምላሳቸውም በትናጋቸው ተጣጋ።
11 ፤ የሰማችኝ ጆሮ አሞገሰችኝ፥ ያየችኝም ዓይን መሰከረችልኝ፤
12 ፤ የሚጮኸውን ችግረኛ፥ ድሀ አደጉንና ረጂ የሌለውን አድኜ ነበርሁና።
13 ፤ ለጥፋት የቀረበው በረከት በላዬ መጣ፤ የባልቴቲቱንም ልብ እልል አሰኘሁ።
14 ፤ ጽድቅን ለበስሁ እርስዋም ለበሰችኝ፤ ፍርዴም እንደ መጐናጸፊያና እንደ ኵፋር ነበረ።
15 ፤ ለዕውር ዓይን፥ ለአንካሳ እግር ነበርሁ።
16 ፤ ለድሀው አባት ነበርሁ፤ የማላውቀውንም ሰው ሙግት መረመርሁ።
17 ፤ የኃጢአተኛውን መንጋጋ ሰበርሁ፥ የነጠቀውንም ከጥርሱ ውስጥ አስጣልሁ።
18 ፤ እኔም አልሁ። በልጆቼ መካከል እሞታለሁ፥ ዕድሜዬንም እንደ አሸዋ አበዛለሁ፤
19 ፤ ሥሬ በውኃ ላይ ተዘርግቶአል፥ ጠልም በቅርንጫፌ ላይ ያድራል፤
20 ፤ ክብሬ በእኔ ዘንድ ታድሶአል፥ ቀስቴም በእጄ ውስጥ ለምልሞአል።
21 ፤ ሰዎች እኔን ሰምተው በትዕግሥት ተጠባበቁ፥ ምክሬንም ለማዳመጥ ዝም አሉ።
22 ፤ ከቃሌ በኋላ አንዳች አልመለሱም፤ ንግግሬም በእርሱ ላይ ተንጠባጠበ።
23 ፤ ዝናብን እንደሚጠብቁ በትዕግሥት ጠበቁኝ፤ የጥቢን ዝናብ እንደሚሹ አፋቸውን ከፈቱ።
24 ፤ እነርሱ ባልታመኑ ጊዜ ሳቅሁላቸው፤ የፊቴንም ብርሃን አላወረዱም።
25 ፤ መንገዳቸውን መረጥሁ፤ እንደ አለቃ ሆኜ ተቀመጥሁ፤ ንጉሥ በሠራዊቱ መካከል እንደሚኖር፥ ኅዘነተኞችን እንደሚያጽናና ኖርሁ።