ምዕራፍ 18

ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ እስከ መቼ ቃልን ታጠምዳለህ? አስተውል፥ ከዚያም በኋላ እንናገራለን።
3 ፤ ስለ ምንስ እንደ እንስሶች ተቈጠርን? ስለ ምንስ በዓይንህ ፊት ረከስን?
4 ፤ ቍጣ ወርሶሃል፤ አንተስ የሞትህ እንደ ሆነ፥ ምድር ስለ አንተ ባድማ ትሆናለችን? ወይስ ዓለት ከስፍራው ይነቀላልን?
5 ፤ የኃጢአተኛ መብራት ይጠፋል፥ የእሳቱም ነበልባል ብልጭ አይልም።
6 ፤ ብርሃን በድንኳኑ ውስጥ ይጨልማል፥ መብራቱም በላዩ ይጠፋል።
7 ፤ የኃይሉም እርምጃ ትጠብባለች፥ ምክሩም ትጥለዋለች።
8 ፤ እግሩ በወጥመድ ትያዛለች፥ በመረብም ላይ ይሄዳል።
9 ፤ አሽክላ ሰኰናውን ይይዛል፥ ወስፈንጠርም ይበረታበታል።
10 ፤ በምድር ላይ የሸምቀቆ ገመድ፥ በመንገዱም ላይ ወጥመድ ለእርሱ ተሰውራለች።
11 ፤ ድንጋጤ በዙሪያው ታስፈራዋለች፥ በስተ ኋላውም ሆና ታባርራቸዋለች።
12 ፤ ኃይሉ በራብ ትደክማለች፥ መቅሠፍትም እስኪሰናከል ተዘጋጅቶለታል።
13 ፤ የሰውነቱ ብልቶች ይጠፋሉ፤ የሞትም በኵር ልጅ ብልቶቹን ይበላል።
14 ፤ ከሚታመንበት ድንኳን ይነቀላል፤ ወደ ድንጋጤም ንጉሥ ያስቸኵሉታል።
15 ፤ በድንኳኑ ውስጥ ለእርሱ የማይሆነው ይኖራል፤ በመኖሪያውም ላይ ዲን ይበተናል።
16 ፤ ሥሩ ከበታቹ ይደርቃል፥ ጫፉም ከበላይ ይረግፋል።
17 ፤ መታሰቢያው ከምድር ላይ ይጠፋል፥ በሜዳም ስም አይቀርለትም።
18 ፤ ከብርሃን ወደ ጨለማ ያፈልሱታል፥ ከዓለምም ያሳድዱታል።
19 ፤ ዘርም ትውልድም በሕዝቡ መካከል አይሆንለትም፤ በመኖሪያውም ውስጥ የሚቀመጥ ሰው አይቀርለትም።
20 ፤ የፊተኞች ሰዎች እንደ ደነገጡ፥ እንዲሁ የኋለኞች ሰዎች ስለ ዘመኑ ይደነቃሉ።
21 ፤ በእውነት የኃጢአተኞች ቤት እንዲሁ ናት፥ እግዚአብሔርንም የማያውቅ ሰው ስፍራ ይህ ነው።